ከሜዳ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ስሙ እየተነሳ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና በሌሎች ሁለት ተጨዋቾች ክስ ቀርቦበት ከመደበኛ ፍርድ ቤት ጥሪ ሲተላለፍበት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይም እንዲታገድበት ትዕዛዝ መተላለፉን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና ከዚህ ቀደም ከደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ በተለያዩ ግለሰቦች ክስ እየተመሰረተበት እንደነበር ይታወሳል። ከዚህ ቀደምም በስድስት የቀድሞ ተጫዋቾች ክስ ተመስርቶበት የነበረው ክለቡም አሁን ደግሞ በተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾች ክስ ተመስርቶበት ከመደበኛ ፍርድ ቤት ጥሪ እንደደረሰው አውቀናል።
የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ በዋለው ችሎትም ክለቡ በቀድሞ ተጫዋቾቹ ተስፋዬ በቀለ እና ደረጄ ዓለሙ በመሐላ ቃል በተደገፈ ያቀረቡትን ክስ እና ማስረጃ ተመልክቶ ግልባጩን ለተከሳሽ (ሀዲያ ሆሳዕና እግርኳስ ክለብ) የላከ ሲሆን ክለቡም መጥሪያው በደረሰው በአስር ቀናት ጊዜ ውስጥ ክሱን ለመከላከል የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተላልፏል። ከሳሽ ሆነው የቀረቡት ሁለቱ ተጫዋቾችም የሕግ አማካሪ ጠበቃ እና የእግርኳስ ስፖርትኞች ሕጋዊ ወኪል በሆኑት አቶ ብርሃኑ በጋሻው ጉዳያቸውን እንደሚከታተሉ ሰምተናል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ሀዲያ ሆሳዕና ከ2013-2014 ከአክሲዮን ከሚከፈለው ድርሻ ላይ እስከ አምስት መቶ ሰባ ስድስት ሺ (576,000) ታግዶ እንዲቆይ ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ደብዳቤ መፃፉን ድረ-ገፃችን ተረድታለች።