​አምስቱ የአዳማ ከተማ ወሳኝ ተጫዋቾች በዛሬው ዕለት ወደ ልምምድ ተመልሰዋል

ያለፉትን 12 ቀናት ከአጋሮቻቸው ጋር ልምምድ ሳይሰሩ የቆዩት አምስቱ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች በከፍተኛ ድርድር ዛሬ ልምምድ ጀምረዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከአንድ ወር በላይ ተቋርጦ የነበረው እና የፊታችን ዓርብ በድሬዳዋ ከተማ በሚቀጥለው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዝግጅቱን ከአስራ ሦስት ቀናት በፊት የጀመረው አዳማ ከተማ ወሳኝ አምስት ተጫዋቾቹ “ቃል የተገባልን የማትጊያ ክፍያ አልተሰጠንም” በሚል ከአጋሮቻቸው ጋር ልምምድ ሳይሰሩ እንደቀሩ ከቀናት በፊት ዘግበን እንደነበር ይታወሳል።

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ክለቡም መቀመጫውን በመዲናይቱ በማድረግ ሱሉልታ ላይ ልምምዱን እየሰራ ቢሆንም ሚሊዮን ሰለሞን፣ ጀሚል ያዕቆብ፣ አብዲሳ ጀማል፣ ቶማስ ስምረቱ እና ሴኩምባ ካማራ በሥልጠናዎቹ ማሳተፍ አልቻለም ነበር። ከላይ እንደተገለፀው ተጫዋቾቹ ልምምድ ባይሰሩም ግን ቡድኑ ያረፈበት ሆቴል በተጠሩበት ቀን ገብተው ነበር። ተጫዋቾቹ በርከት ያሉትን ቀናት ልምምድ ባይሰሩም ከትናንት በስትያ የክለቡ አመራሮች አዳማ ድረስ ጠርተዋቸው ውይይት እንዳደረጉ የሰማን ሲሆን ሁለቱም አካላት በቃል ደረጃ መግባባት ላይ እንደደረሱ ተነግሮናል። ክለቡም በቅርቡ ክፍያውን እንደሚፈፅም የገለፀላቸው መሆኑን ስናውቅ ተጫዋቾቹም ወደ ድሬዳዋ ከማምራታቸው በፊት ገንዘባቸው በእጃቸው ካልደረሰ ወደ ስፍራው ላለማቅናት አቋም እንደያዙ አውቀናል።


ምንም እንኳን ተጫዋቾቹ እና አመራሮቹ ከትናንት በስትያ ውይይት ቢያደርጉም አምስቱም ትናንት ልምምድ ሳይሰሩ በዛሬው ዕለት ልምምድ መስራት መጀመራቸውን ድረ-ገፃችን ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።