በዓምላክ ተሰማ ነገ የሚደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ይመራል

በአፍሪካ ዋንጫው ላይ በዳኝነት እየተሳተፈ የሚገኘው በዓምላክ ተሰማ የውድድሩ አዘጋጅ ሀገር ደጋፊዎች በጉጉት የሚጠብቁትን ጨዋታ እንዲመራ እንደተመደበ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

24 የአፍሪካ ሀገራትን አሳትፎ በአሁኑ ሰዓት 16 ሀገራትን ብቻ ያስቀረው ተጠባቂው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከዛሬ ጀምሮ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎቹን ማከናወን ይጀምራል። ምሽት 1 እና 4 ሰዓትም ቡርኪና ፋሶ እና ጋቦንን እንዲሁም ናይጄሪያ እና ቱኒዚያን የሚያፋልም ይሆናል። ነገም ይሁ ጥሎ ማለፍ ቀጥሎ ሲደረግ ጊኒ ከጋምቢያ እንዲሁም ካሜሩን ከኮሞሮስ የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቅ ሲሆን ምሽት አራት ሰዓት በኦሌምቤ ስታዲየም የሚደረገውን የውድድሩ አዘጋጅ ሀገር ካሜሩን እና በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረኩ ተሳትፋ አስገራሚ ግስጋሴ እያደረገች የምትገኘው ኮሞሮስ የሚያደርጉትን ጨዋታ ኢትዮጵያዊው ዳኛ በዓምላክ ተሰማ በመሐል ዳኝነት እንደሚመራው ድረ-ገፃችን አረጋግጣለች።

ከዚህ ቀደም ሴኔጋል እና ጊኒ ያደረጉትን ጨዋታ በመሐል አልቢትርነት የመራው በዓምላክ ናይጄሪያ ከግብፅ እንዲሁም ግብፅ ከሱዳን ሲፋለሙ በመጀመሪያ የቪ ኤ አር ዳኝነት ተሳትፎ እንደነበር ይታወሳል። አሁን ደግሞ ውድድሩ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ባለበት ሰዓትም ኢትዮጵያዊው ዳኛ ጨዋታዎችን እንዲመራ ተደርጓል።

በዚህም ከላይ እንደገለፅነው ካሜሩን እና ኮሞሮስ የሚያደርጉትን ጨዋታ ከሞዛምቢክ እንዲሁም ኬኒያ ከመጡት አርሴኒዮ ቻድሪኩይ ማሪንጉዌል እና ጊልበርት ኪፕኮች ቼርዮት በመስመር ረዳት ዳኝነት እንዲሁም ከሲሸልሳዊው በርናርድ ሄንስል ካሚሊ አራተኛ ዳኝነት እየታገዘ ጨዋታውን እንደሚከውን አውቀናል። የጨዋታው ኮሚሽነር ከኮንጎ ሲሆኑ ከደቡብ አፍሪካ፣ ኬኒያ እና አንጎላ የተመረጡት ዳኞችም የቪ ኤ አር ክፍል ውስጥ እንደሚሆኑ ተመላክቷል።