👉”ባቀድነው ልክ ባለማሳካታችን የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን” ባህሩ ጥላሁን
👉”ከእቅዳችን አንፃር ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ባንችልም መልካም ተሳትፎ ነበረን ብዬ ነው የማስበው” ውበቱ አባተ
👉”…አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ሆነው ይቀጥላሉ” ባህሩ ጥላሁን
👉”ሀገራችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ላይ አደለችም” ውበቱ አባተ
👉”በአጠቃላይ በቁጥራዊ ነገሮች ጥሩ ነበርን” ውበቱ አባተ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካሜሩን አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው የአህጉሪቱ ትልቁ ውድድር ላይ ተሳትፎ ከምድቡ አንድ ነጥብ ብቻ በማግኘት ከውድድሩ መሰናበቱ ይታወቃል። ካሜሩን ቀድሞ ደርሶ ቀድሞ የወጣው ብሔራዊ ቡድኑን አስመልክቶም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ወሎ ሰፈር በሚገኘው ጽሕፈት ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ አዘጋጅቷል። በመግለጫውም የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በካሜሩን ስለነበራቸው ቆይታ ማብራሪያ ሲሰጡ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ደግሞ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሀሳብ ሰጥተዋል። በቅድሚያም አቶ ባህሩ መድረኩን አስጀምረው ተከታዩን አጭር ንግግር አድርገዋል።
“ወደ ካሜሩን ስንጓዝ ከመንግስት 35 ሚሊዮን ብር ተሰጥቶን ነበር የሄድነው። እንደ ፌዴሬሽን ከምድብ ለማለፍ አቅደን ነበር። ባቀድነው ልክ ባለማሳካታችን ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን።” ብለዋል። በማስከተል ደግሞ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከተጫዋች ጥሪ ጀምሮ ሦስቱም ጨዋታዎችን የተመለከተ ሀሳብ ማጋራት ይዘዋል።
“የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ታህሣሥ 15 አልቆ በ17 ነው ወደ ካሜሩን የሄድነው። ወደ ስፍራው ስንሄድ 28 ተጫዋቾችን ጠርተን ነበር። በቅድሚያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 25 ተጫዋቾችን ብቻ ያዙ ስላለ 3 ተጠባባቂ አድርገን ዝርዝሩን አስገብተናል። ከዛ ግን ሦስቱን እንድናካትት ስለተነገረን 28 ተጫዋች ይዘናል። ግን ከኤርፖርት ስንነሳ አንድ ተጫዋች ኮቪድ-19 ስለተያዘ እሱን ትተን ሄደናል። የተውነውንም ተክተናል። ካሜሩን ስንደርስ ደግሞ 2 ተጫዋች እና 1 የአሠልጣኝ ቡድን አባል ኮቪድ ተይዘው ማቆያ ገብተዋል።
“ዝግጅታችንን ካሜሩን ስናደርግ ቢበዛ 3 ቢያንስ 2 የአቋም መተሻ ጨዋታዎችን ለማረግ አስበን ነበር። ግን ካሜሩን አንድ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ብቻ ነው ያደረግነው። ከሱዳን ጋር ልናደርግ ከነበረው ጨዋታ በፊትም 5 ተጫዋቾች እና 2 የአሠልጣኝ ቡድን አባላት በኮቪድ-19 ተይዘው ነበር። በሌላ በኩል ሽመልስ በቀለ የጡንቻ ህመም አጋጥሞት እንዲሁም ፋሲል ገብረሚካኤል በትከሻ ጉዳት በውድድሩ አልተሳተፉም። ሙጂብ ደግሞ በመጨረሻው ጨዋታ በደረሰበት ህመም አልተሳተፈም።” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት አሠልጣኙ ከሦስቱ የምድብ ጨዋታዎች ጋር ተያይዞ ያሉ ነጥቦችን ደግሞ በተከታይነት ማንሳት ቀጥለዋል።
“በመጀመሪያው ጨዋታ መቆጣጠር በማንችለው መንገድ በጊዜ ተጫዋቻችን በቀይ ወጥቷል። ከካሜሩን ጋር ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ነበርን። ከእረፍት መልስ ግን የተጋጣሚን ጫና እና ሽግግር ከመቋቋም ጋር ተያይዞ በተፈጠሩ ትናንሽ ክፍተቶች ጨዋታው አምልጦናል። ከቡርኪና ፋሶ ጋር ደግሞ በሁሉም ነገሮች ጥሩ እንደነበርን የሚያሳዩ ቁጥራዊ ማሳያዎች አሉ። በማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ የታየው የቡድኑ ብቃት በዋናው ውድድሩ ላይ ነበረ ማለት ግን አንችልም።
“በአጠቃላይ በቁጥራዊ ነገሮች ጥሩ ነበርን። በዚህ ውድድር በአብዛኛው በሀገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን የያዝን እኛ ነን። የእኛ ዳሰሳ የሚያሳየው ሀገራችን በቅርብ ጊዜ ወደሚፈለገው ተፎካካሪነት እንደምትደርስ ነው። ከዚህ ውጪ ከሌሎቹ ሀገራት የምንርቅበት መንገድም አለ። ይህ በሁለት ሳምንት ብቻ በሚሰራ ልምምድ ግን አይቀረፍም።”
እጅግ በርካታ የብዙሃን መገናኛ አባላት የተገኙነት ጋዜጣዊ መግለጫ ቀጥሎ አሠልጣኝ ውበቱ “ከእቅዳችን አንፃር ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ባንችልም መልካም ተሳትፎ ነበረን ብዬ ነው የማስበው” ካሉ በኋላ ከፌዴሬሽኑ ጀምሮ ሚዲያ፣ መንግስት እና የስፖርት ቤተሰብ ድጋፍ ስላደረገላቸው ምስጋና አቅርበው ሀሳባቸውን ቋጭተዋል። ለሁለት ሰዓት የተጠጋ ቆይታ የነበረው መግለጫውም በተከታይነት ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች እንዲነሱ በር ከፍቶ ጥያቄዎች ለሁለቱ አካላት መቅረብ ጀምሯል።
ከዝግጅት ጋር ተያይዞ ፌዴሬሽኑ አስቧቸው ስለነበራቸው ጉዳዮች?
“ቡድኑ ወደ ስፍራው ሲያመራ 3 የወዳጅነት ጨዋታዎችን እናደርጋለን ብለን ነበር። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አፍሪካ ዋንጫውን የተመለከተ ዝግጅት የጀመረው ማለፋችንን ካወቅን ጀምሮ ነበር። በተለይ ደግሞ እጣው ከወጣ በኋላ። በተለይ ከሳውዲ አረቢያ ፌዴሬሽን ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት ስላለን ዝግጅታችንን እዛ ብናረግ ሙሉ ወጪያችን እንደሚሸፈን እና የተለያዩ ቡድኖችም እዛ ስለሚዘጋጁ ጨዋታ እናረጋለን የሚል ሀሳብ ነበረን። ግን ስኬታማ መሆን አልተቻለም። ምንም እንኳን ፌዴሬሽኑ (የሳውዲ አረቢያ) ደስተኛ ቢሆንም ሀገሪቷ ከጉዞ እቀባ ጋር ተያይዞ ባላት ትዕዛዝ እቅዳችን አልተሳካም። ከዛ በሁለተኛ እቅድ ጊኒ እና ጋቦን ሄደን ለመዘጋጀት አሰብን። ግን እሱም እንደማይሆን አወቅን። ከዛ ውድድሩ የሚደረግበት ቦታ ለመሄድ ወሰንን።
“ዝግጅት እና የአቋም መፈተሻ ጨዋታን በተመለከተ አንድ የፊፋ ኤጀንት ነበር። እሱም ልምድ ያለው ኤጀንት ነው። ከእርሱ ጋር በመነጋገር ሦስት ጨዋታዎችን ለማድረግ አስበን ነበር። በዚህም ከሱዳን፣ ዚምባቡዌ እና ሞሮኮ ጋር ለመጫወት ተነጋገርን። ከሱዳን ጋር ከተጫወትን በኋላ ከዚምባቡዌ ጋር ለመጫወት ከእነርሱም ከእኛም በኩል ፍላጎት አልነበረም። ይህም የሆነው ቀድመን ስለተገናኘን ነው። ሞሮኮ ደግሞ ዘግይቶ ነው ካሜሩን የመጣው። ከጊዜ ጋር ተያይዞ እና እነሱ ሌላ እቅድ ስለነበራቸው ከእነርሱ ጋር ጨዋታ ማድረግ አልተቻለም። ከዚህ ውጪ በካሜሩን ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ጨዋታ ለማድረግ ታስበቦ ነበር። ግን አሠልጣኞቻችን ጋር ፍላጎት አልነበረም።” ባህሩ ጥላሁን
የወዳጅነት ጨዋታ ስላለማድረጋቸው?
“የወዳጅነት ጨዋታ ይጠቅማል። እንደ ዩጋንዳ አይነት ቡድኖች ለ2023 ውድድር ጨዋታ ካሁኑ እያደረጉ ነው። ከዋናው ጨዋታ በፊት ጥሩ ጨዋታ ብናገኝ ይጠቅመን ነበር። ይህንን አለማድረጋችን በዋናው ጨዋታ ራሳችንን እየፈተሽን እንድንሄድ አድርጎናል።” ውበቱ አባተ
በሦስቱ ጨዋታዎች ስለነበረው የተጫዋች ምርጫ?
“ጨዋታዎቹ የየራሳቸው ባህሪ አላቸው። ልምምድ እና የተቃራኒ ቡድን ታሳቢ ይደረጋሉ። በመጨረሻው ጨዋታ ይሁን እንዳሻውን ያስገባነው በሁለት ሰው በተከላካይ አማካይ ቦታ ለመጫወት ሳይሆን ቦታው ሀይል ስለሚፈልግ ነው። የራሳችንን ጨዋታ ከመጫወት ባለፈ ተጋጣሚን ለመቆጣጠር በማሰብ ነው። ከሽንፈት ከመምጣታችን እና እርስ በእርስ ካለን የቀደመ ግንኙነት አንፃር ቡድኑ በጨዋታው አድጎ ነበር።” ውበቱ አባተ
ወደ ውድድሩ ሲያመሩ የነበራቸው ዕቅድ አለመሳካቱ?
“ማግኘት በሚገባ ነጥብ (Expected point) ኢትዮጵያ የተሻለ ነጥብ ነበራት። ወደ አራት የሚጠጋ ነጥብ ነበራት። አምስት ነጥብ በአስተማማኝ ደረጃ ወደ ቀጣይ ዙር ያሳልፋል። አራት ነጥብ ደግሞ ሀምሳ ሀምሳ የማሳለፍ ዕድል አለው። ሦስት ነጥብ ደግሞ መጠነኛ ጭላንቅለል አለው። ከዚህ መነሻነት በተሰራ ዓለም አቀፋዊ ጥናት ቡድናችን ያገኘው ነጥብ ይህ ነው። በእንዳልኩት ሀገራችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ላይ አደለችም። የምንፈራው ቡድን የለም። ግን ሁሉንም እናከብራለን። እኛም አቅም አለን።” ውበቱ አባተ
ስለ ቡድኑ የፊት መስመር?
“ሦስቱም ተጫዋቾች ከመስመሩ ወደ ውስጥ ገበተው እንዲጫወቱ ነው ፍላጎታችን። መስመሩን ደግሞ በመስመር ተከላካዮቻችን ለመሸፈን ነው ሀሳባችን። በሁለተኛው ጨዋታ ጌታነህ ጉንፋን ነገር ስለነበረት አቡበከርን በሀሰተኛ 9 ቁጥር እንዲጫወት አድርገነዋል። ይህ በተወሰነ መልኩ ሰርቶልናል። በአጠቃላይ ግን ቡድናችን ከኳስ ውጪ ትንሽ ደከም ያለ ነበር።” ውበቱ አባተ
ስማቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እየተያያዘ ስለመሆኑ?
“ወቅቱ አደለም። ኮንትራት ላይ ነኝ። በግሌም የማቀው ነገር የለም። ወሬ ነው። የተጨበጠ ነገር አይደለም።” ውበቱ አባተ
ተጋጣሚን ስለማየት?
“እንደ ቡድንም ሆነ እንደ ግል፣ ሲከላከሉም ሆነ ሲያጠቁ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ጊዜ ሰጥተን ለማየት ሞክረናል። ከምድባችን አንፃር ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምሮ ቢሳካልን ኖሮ 4 ነጥብ ብናገኝ የሚል ሀሳብ ነበር።” ውበቱ አባተ
ስለ ተጫዋቾች ተክለ ሰውነት?
“የእኛ ተጫዋቾች አሁን ባላቸው አካላዊ ቁመና ላይ መጠንከር አለባቸው። ግንኙነቶች ላይ ክፍተት አለ። በተለይ ደግሞ የአየር ላይ ግንኙነቶችን ብዙ ማሸነፍ አንችልም። ይሄ ስራ ግን የሳምንት እና የአስራ አምስት ቀን ስራ አደለም። ተጫዋቹ ራሱ ላይ ሊሰራ ይገባል። ብሔራዊ ቡድን ላይ በ15 ቀን ይሄንን ስራ መስራት አንችልም። መጫወት የምንፈልገውን እንድንጫወት ራሱ የሚጠበቅ ፊትነስ ያስፈልገናል።” ውበቱ አባተ
ስለትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች?
“እንደ ጋምቢያ ኮሞሮስ አይነት ቡድኖችን በአፍሪካ ዋንጫው ያሳዩን ነገር አለ። ሀገራችን ወደዚህ እንድትመጣ በመጀመሪያ የፓስፖርቱ ጉዳይ መፈታት አለበት። ይህ የአሠልጣኙ ወይም የፌዴሬሽኑ ጉዳይ ብቻ አደለም። ይህ እንደ ሀገር ካለ ፖሊሲ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ነው። ጥምር ዜግነት ስለማይፈቀድ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን መጠቀም አንችልም። እኛ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋገር ሞክረናል። ሚዲያውም እንደ አጀንዳ ይዞ ጉዳዩን የሚመለከተውን አካል ጋር ለማድረስ መጣር አለበት።” ባህሩ ጥላሁን
ወደ ስፍራው ጋዜጠኞች ይሄዳሉ ተብሎ ስለቀረበት ጉዳይ?
“ከሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን ጋር በገባነው ውል መሰረት ደጋፊ እና ጋዜጠኞች እንዲጓዙ ተነጋግረን ነበር። ይህ የሚሆነው ደግሞ ስፖንሰር አድራጊዎች ከተገኙ ነበር። የጋዜጠኞች ምርጫን እኛ አድርገን ይዞ እንዲሄድ ነበር ሀሳባችን። የተሰጠውን ምክንያት እኛ ባናምንበትም አለመሳካቱን ባለቀ ሰዓት አውቀናል። ምንም ማድረግ አልተቻለም።” ባህሩ ጥላሁን
አሠልጣኙ ስላላቸው ቀጣይ ቆይታ?
“ውበቱ አባተ ለሁለት ዓመት ነው የፈረመው። ያስቀመጥናቸው ግዴታዎች ነበሩ። በዓለም ዋንጫው የመጨረሻ አስሮች ውስጥ ከመድረስ ባለፈ ሁሉም ተፈፅሟል። ስለዚህ ኮንትራቱን እናከብራለን። እስከ ኮንትራቱ ማብቂያ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ሆነው ይቀጥላሉ።” ባህሩ ጥላሁን