​”ማኅበራዊ ገፆች ላይ እንዳለው ኮብልስቶን ይዞ የተቀበለን ሰው የለም” ውበቱ አባተ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ በአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑ ያስመዘገበውን ውጤት ተከትሎ የህዝቡን አቀባበል ስላገኙበት መንገድ ሀሳብ አጋርተዋል።

በቅርብ ጊዜያት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከተሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ምናልባት ረጅሙ በሆነው የዛሬው መግለጫ ላይ የተነሱ ሀሳቦችን ከደቂቃዎች በፊት ያቀረብን ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫው ያስመዘገበውን ውጤት ተከትሎ ስለነበረው የአቀባበል ሥረ-ስርዓት እና ስለ ህዝቡ ግብረ መልስ ተጠይቀው የሚከተለውን ብለዋለል።


“ወደ ካሜሩን ስንሄድም ሆነ ስንመጣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። ተደብቀንም አልገባንም። ይህ ብሔራዊ ቡድን ነው። የሁሉም ቡድን ነው። ስንሄድ መንግስት በክብር ነው የሸኘን። ስንመለስም አምባሳደሮች ሳይቀር መጥተው ተቀብለውናል። አንዳንድ ጋዜጠኞች ጋር ቡድኑ ሌላ ነው። አንዳንዱ ጋር ደግሞ ሌላ። ህዝቡ ጋር ደግሞ ሌላ ነው። እኔ በግሌ ሀገሬ ገብቼ ፎቶ ስነሳ ነበር። የህዝቡ አቀባበል እንዴት ነው ካልከኝ ህዝቡ ከዚህ በተሻለ እና እኛም በምንፈልገው ደረጃ አሳክተን ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር። የተቀመጥነውም ለዚህ ስለሆነ። ይህ የእኔ ብቻ ፍላጎት ሳይሆን የተጫዋቾቹም ፍላጎት ስለሆነ። ይህ ተሳክቶ ወደ ቀጠቀዩ ዙር አልፈን ቢሆን ኖር ደስ ይለኝ ነበር። አሁን ባለውም ነገር ቢሆን ግን ከመጥፎው ነገር በተሻለ በጣም ብዙ ጥሩ ግብረ መልሶች ከበርካታ ሰዎች ደርሶናል። ማኅበራዊ ገፆች ላይ (ቲክ ቶክ ላይ ምናምን) እንዳለው ኮብልስቶን ይዞ የተቀበለን ሰው የለም። 


“እኔ አንድ ሰው ነኝ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጉዳይ ከአንድ ሰው የዘለለ ጉዳይ ነው። ኩራት ነው። ብሔራዊ ቡድኑን በማሰልጠን የምታተርፉት ነገር ኩራት ነው። ለልጅ ልጅ የሚሆን ኩራት። ከዚህ ውጪ ከክለብ የተሻለ ሳንቲም የለውም። እንደተባለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ብገባ እኔ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ አገኛለው። ኑሮዬን በደንብ እገፋበታለው። ብሔራዊ ቡድን ላይ በመሆኑ ይሄንን እያጣሁበት ነው። ማንም እዚህ ቦታ ላይ ቢቀመጥ እንደግፈው። ከአንድ ቀን በፊት እሁድ ሰርግ ነበረ። ከሙሽራው ያልተናነሰ ፎቶ ተነስቻለው። ምንም ቅር ሳይለኝ። ይህ ህዝብ ተደስቶ ነው ወይ ካልከኝ አደለም። ከዚህ በላይ ሊደሰት ይገባል። ግን ደግሞ መርሳት የሌለብን ነገር ይዘነው በሄድነው ነገር ነው። ይዘን የሄድነው ነገር እንደሚያራምደን አምናለው። ግን እስከ የት ያራምዳል የሚለውን እንደ ሀገር ማየት አለብን። ሊጋችንን እና ፉክክሩን ማሳደግ አለብን። ተጫዋቾችንም ማሳደግ አለብን። አሁን ካለን ስብስን ግን ይሄ ብቻ ነው ወይ ካንተ የሚጠበቀው ካልከኝ ቢያንስ ትንሽ መግፋት እንችል ነበር።”