​የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ መሪ በአመራሮቹ ማበረታቻ ቃል ተገባለት

በኢትዮጵያ እግርኳስ ገናና ስም ያለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ካደገ ለቡድኑ አባላት ከፍተኛ ሽልማት እንደሚሰጥ ዛሬ በተከናወነ የምሳ ግብዧ ይፋ ሆኗል።

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2010 ላይ የወረደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለፉትን ዓመታት በሁለተኛው የሊግ እርከን ተፎካካሪ በመሆን ዳግም ወደ ሊጉ ብቅ ለማለት ሲሞክር እንደነበር ይታወሳል። ባሳለፍነው ዓመትም የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ አለመሳተፋቸውን ተከትሎ በተፈጠ ዕድል ከዋናው ውድድር በኋላ ሌላ አቋራጭ መንገድ አገኝቶ የነበረው ቢሆንም ውጥኑ ሳይሳካ ቀርቶ ነበር። ዘንድሮ ግን ይህንን ግብ ለማሳካት በምድብ ሀ ተደልድሎ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በመጀመሪያው ሊግ ውድድርም አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ በ21 ነጥቦች በመሪ ቦታ ላይ ተቀምጧል። የቡድኑን አዎንታዊ ውጤት በመንተራስም የክለቡ አመራሮች በዛሬው ዕለት በሂልተን ሆቴል የምሳ ግብዧ ያከናወኑ ሲሆን ቡድኑም ወደ ሊጉ ካደገ ለተጫዋቾች እና አሠልጣኞች ሽልማት እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።

የክለቡን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጫላ አማንን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች፣ ተጫዋቾች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት በተገኙበት መርሐ-ግብር ላይ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ እጅጉ መድረኩን በመምራት የቦርድ ሰብሳቢው የመክፈቻ ንግግር እንዲያረጉ ጋብዘዋል። ሰብሳቢውም “ዘንድሮ 60ኛ ዓመታችንን እናከብራለን። ይህንን አንጋፋ ክለብም በዚሁ ዓመት ከማይመጥነው ቦታ እንድታሳድጉ ዕድሉን አግኝታችኋል። ተጠቀሙበት።” ካሉ በኋላ ምድባቸውን እየመሩ በመሆናቸው ደስታ እንደተሰማቸው አመላክተው በውድድር ዓመቱ ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገ የ10 ሚሊዮን ብር ሽልማት እንደሚሰጡ ተናግረዋል። ቡድኑ አንድ ጨዋታ እየቀረው ካደገ 1፣ ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት ካደገ 2 እንዲሁም ሦስት ጨዋታዎች እየቀሩት ካደገ 3 ሚሊዮን ተጨማሪ ሽልማት እንደሚኖር ገልፀዋል።

ከአቶ ጫላ አማን በመቀጠል የምሳ መርሐ-ግብር የተከናወነ ሲሆን ከዛ በኋላ ደግሞ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ክፍሌ ቦልተና የተሰማቸውን ስሜት በተከታዩ መልኩ አጋርተዋል። “ዓምና በአጭር ጊዜ ተዘጋጅተን ጥሩ ውጤት ነበር ያመጣነው። ዘንድሮ ደግሞ ጥቂት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን እና ወጣት ተጫዋቾችን አሳድገን ውጤታማ ለመሆን እየጣርን ነው። ክለቡም እየረዳን ነው። ከላይ እስከ ታች ድረስ ያለው ሰው ቡድኑን ለማሳደግ የሚጥር ነው። እኔም ያደኩበት ክለብ ነው። በደንብ ሰርተን 100% እናልፋለን ብዬ አስባለው። ቃልም እገባለውም። እዚህ ስለደረስንም ተጫዋቾቼንም አመሰግናለው።” ብለዋል። በመጨረሻም ተጫዋቾችን ወክለው ምንያህል ተሾመ እና ሳሙኤል ታዬ ክለቡን ለማሳደግ ቁርጠኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።


ያጋሩ