​የሰበታ ከተማ ረዳት አሠልጣኞች ከክለቡ ጋር አይገኙም

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው ሰበታ ከተማ ሁለቱን ረዳት አሰልጣኞች ሳይዝ ድሬዳዋ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ካደረጋቸው ዘጠኝ መርሐ-ግብሮች ሰባት ነጥቦችን በመስብሰብ ከደረጃው ግርጌ ከፍ ብሎ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሰበታ ከተማ በቀጣይ በድሬዳዋ ለሚደረገው የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ካለበት ደረጃ የተሻለውን ይዞ ለማጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል፡፡ በአሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚሰለጥነው ይህ ክለብ አሁን ላይ ሁለቱን ረዳት አሠልጣኞቹን ሳይዝ ድሬዳዋ መድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ምንም እንኳን አሠልጣኞች በምን ምክንያት ከክለቡ ጋር እንደሌሉ ወደ ክለቡ አካባቢ ለመጠየቅ ጥረት ብናደርግም ምላሽ የሚሰጠን አካልን ማግኘት አልቻልንም። ድረ-ገፃችን እንዳገኘችሁ መረጃ ከሆነ ግን ከክለቡ ጋር ረዘም ያሉ ዓመታትን በረዳት አሠልጣኝነት ያገለገሉት ብርሀን ደበሌ እና በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሌላኛው ረዳት አሠልጣኝ የሆኑትን ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማሪያምን ክለቡ በማገዱ እንደሆነ ተረድታለች።

ከዚህ ጉዳይ ጋር የሚኖሩ አዳዲስ ጉዳዮች ካሉ ተከታትለን ወደ እናንተ የምናደርስ ይሆናል፡፡

 

ያጋሩ