የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅቱን ጀምሯል

ለዓለም ዋንጫ ማጣርያ አራተኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ታንዛኒያን ገጥሞ አንድ ለምንም ተሸንፎ የተመለሰው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅቱን ጀምሯል።

ለኮስታሪካው የሴቶች ከ20 ዓመት የዓለም ዋንጫ ለማለፍ አፍሪካን የሚወክሉ ሁለት ሀገራትን ለመለየት ለአራተኛው ዙር ማጣርያ የደረሰው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ታንዛንያ አቅንቶ ከዕረፍት በኃላ በተቆጠረች አንድ ጎል መሸነፉ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድን ሰኞ አመሻሽ አዲስ አበባ ሲደርስ የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል የተደረገለት ሲሆን ቡድኑ በቀጥታ ወደ ጁፒተር ሆቴል በማምራት ለሁለት ቀናት እረፍት እንዲያደርግ ተደርጓል።

ትናንት የካፍ ልህቀት ማዕከል ማረፊያውን ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ በዛሬው ዕለት ለመልሱ ጨዋታ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ ዝግጅቱን ጀምሯል። ለአንድ ሰዓት ተኩል በፈጀው የዛሬው ልምምድ በታንዛንያው ጨዋታ ወቅት ባጋጠሙ ታክቲካል ክፍተቶች ዙርያ አሰልጣኝ ፍሬው ከኳስ ጋር ሰፊ ስልጠና ሲሰጡ ተመልክተናል። የኃላ መስመር አራቱም ተከላካዩች ብዙአየሁ ታደሰ፣ ብርቄ አማረ ቤተልሔም በቀለ እና አንበሏ ናርዶስ ጌትነት ለብቻቸው ተነጥለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲሰሩ አስተውለናል። ወደ ታንዛንያ ያቀኑት 20 ተጫዋቾች በሙሉ በተሳተፉበት በዚህ ልምምድ ሁሉም የቡድኑ አባላት በመልካም ጤንነት ሲገኙ የግብጠባቂዎች አሰልጣኝ ፀጋዘአብ አስገዶም በዚህ የልምምድ ወቅት አለመገኘታቸውን አይተናል።

ውጤቱን መቀልበስ እንደሚቻል እና አካዳሚው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የአካዳሚው ዋና ዳሬክተር አቶ አንበሳው እንየው በልምምድ ወቅት ተገኝተው ከአሰልጣኝ ፍሬው ጋር መጠነኛ ውይይት አድርገዋል። በዚህ መልኩ ልምምዱን የሚቀጥለው ብሔራዊ ቡድኑ ምን አልባት ከቀናት በኋላ የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።