ጎፈሬ የትጥቅ አምራች ኩባንያ ለአንደኛ ሊጉ ክለብ ድጋፍ አደረገ

ሀገር በቀል የትጥቅ አምራች ኩባንያ የሆነው “ጎፈሬ” ዋና ስራ አስኪያጅ እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል ሃምሳ ሺህ ብር በላይ ዋጋ የሚያወጣ የእግርኳስ ትጥቅ ድጋፍ ለወሊሶ ከተማ ቡድን አድርገዋል።

በሀገራችን የስፖርት ዘርፍ ያለውን የትጥቅ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ውጥን ሰንቆ የተነሳው ግዙፉ የሀገር በቀል የትጥቅ አምራች ኩባንያ የሆነው “ጎፈሬ” በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ከገባ ወዲህ በፍጥነት ተቀባይነት በማግኘት የገበያ ድርሻውን በማሳደግ በስፖርት የትጥቅ አቅርቦት ዘርፍ በሀገራችን ቀዳሚው ተቋም መሆን ችሏል።

በትጥቆች አቅርቦት ገበያው ላይ በስፋት እየተሳተፈ የሚገኘው ኩባንያው ከዚህ ባለፈ በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍም የድርሻውን ለመወጣት እንዲሁ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል ፤ የዚህ ሂደት አንዱ አካል በሆነው እና በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ተካፋይ ለሆነው እና በቅርቡ ጉዳት ለደረሰበት ለወሊሶ ከተማ ስፖርት ክለብ የድርጅቱ ዋና ስራአስኪያጅ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ከሃምሳ ሺ ብር በላይ ግምት የሚወያወጣ ትጥቅ ድጋፍ አድርገዋል።

የወሊሶ ከተማ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ቢንያም ባህሩ ከድጋፉ በኃላ ለሶከር ኢትዮጽያ እንደገለፁት ከሆነ ለተደረገላቸው የትጥቅ ድጋፍ ኩባንያውን ያመሰገኑ ሲሆን ፤ የተደረገው የትጥቅ ድጋፍ ከዚህ ቀደሙ እጅግ የተለየ እና እግር ኳስ የሚፈልገውን መስፈርት ያሞላ ነውም ብለዋል።

ስራአስኪያጁ አያይዘውም ይህ በወሊሶ ከተማ ስፖርት ክለብ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በደረጃውም ሆነ በህትመት ጥራቱ የላቀ የስፖርት ትጥቅ እንደሆነ በመግለፅ በክለቡ ስም እንዲሁም በወሊሶ ከተማ ደጋፊዎች ስም የጎፈሪ ትጥቅ አምራች ኩባንያ ስራአስኪያጅ ለሆኑት አቶ ሳሙኤል እጅግ ከፍ ያለ ምስጋናን አቅርበዋል።

“ጎፈሬ” በቀጣይ መሰል ድጋፉችን አቅም በፈቀደ መልኩ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆነ እና ለሀገራችን የስፖርት ዘርፍ እድገት የተቻለውን ጥረት እንደሚያደርግ የኩባንያው የበላይ ሀላፊዎች በትጥቅ ርክክቡ ወቅት ገልፀዋል።

ያጋሩ