የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት ጨዋታች ነገ ድሬዳዋ ላይ መደረግ ሲቀጥሉ 16ቱም የቡድን መሪዎች አመሻሽ ላይ በሊጉ የበላይ አካል ሰብሳቢነት ውይይት አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይነት የሚከናወነው የሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ ዕርከን ውድድር በሀዋሳ ከተማ 9 ሳምንታትን ካከናወነ በኋላ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል። ብሔራዊ ቡድናችንም ከአህጉራዊ መድረኩ በጊዜ መሰናበቱን ተከትሎ ውድድሩ ከአንድ ወር ከአምስት ቀናት በኋላ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ድሬዳዋ ከተማ በነገው ዕለት መከናወን ይጀምራል።
በዓመቱ መጀመሪያ በተያዘ መርሐ-ግብር የሊጉን ጨዋታዎች በሦስተኝነት ለማከናወን ተራ ተሰጥቶት የነበረው ድሬዳዋ አዳማ ከተማ በተሰጠው ቀነ ገደብ የመብራት ፓውዛ እና የመጫወቻ ሜዳ ጉዳዮችን ሳያሟላ ቀርቶ ውድድሩን ለማስተናገድ ዕድሉን አግኝቷል። ይህንን ያልታሰበ ዕድል ለመጠቀምም የመጫወቻ እና የመለማመጃ ሜዳዎች እንዲሁም ዋናው ሜዳ ለምሽት ጨዋታዎች እንዲሆን የፓውዛ ገጠማን አገባዷል። የሊጉ ተሳታፊ ክለቦችም በዛሬው ዕለት ተጠናቀው በከተማዋ ገብተዋል።
ሶከር ኢትዮጵያ ስፍራው ተገኝታ የስታዲየሙን የቀን እና የምሽት አሁናዊ ሁኔታ በምስሎች ያቀረበች መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የቅዳሜ እና እሁድ ጨዋታዎችም የሰዓት ሽግሽግ (9 እና 12 ሰዓት) እንደተደረገባቸው ገልፃለች።
የውድድሩ የበላይ አካል የሆነው አክሲዮን ማኅበር ደግሞ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ የ16ቱንም ክለብ የቡድን መሪዎች በራስ ሆቴል ሰብስቦ ያለፉትን 9 ሳምንታት በሀዋሳ የተደረጉትን ጨዋታዎች ተንተርሶ ሪፖርት በማቅረብ ከድሬዳዋ ከተማም ምን እንደሚጠበቅ ገለፃ ተደርጓ አጠር ያለ ውይይት ተደርጓል። ከዚህ ውጪ ከከተማዋ መስተዳደርም ተወካይ መጥቶ ውድድሩ በደመቀ ሁኔታ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የውድድር እና ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ በመሩት መድረክ ላይ የየክለቦቹ ተወካዮች በከተማው የተደረገላቸውን አቀባበል በከፍተኛ ሁኔታ አመስግነው በልምምድ ሜዳዎች ላይ በትኩረት እንዲሰራ ሲያሳስቡ አድምጠናል። ሰብሳቢውም ክለቦች የራሳቸው የቤት ስራቸውን አጠናክረው እንዲሰሩ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረው መልካም የውድድር ጊዜ እንዲኖር መልካም ምኞት ተመኝተው መርሐ-ግብሩ ተገባዷል።
በተያያዘ ዜና ከነገ ጀምሮ የሚደረጉትን የመጪው ሦስት የጨዋታ ሳምንታት መርሐ-ግብሮችን (10፣ 11 እና 12) አስር ዋና አስር ረዳት ዳኞች እንዲሁም ስድስት ኮሚሽነሮች እንደሚመሩት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የሚዲያ ሀላፊ አቶ ሙሉጌታ ነግረውናል።