ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ የድሬዳዋ ቆይታውን በድል ጀምሯል

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 2-0 መርታት ችሏል።

ሊጉ ወደ እንቅስቃሴ የተመለሰበት የቡና እና ሀዋሳ ጨዋታ በጥሩ ፉክክር የጀመረ ነበር። በጨዋታው ቡናዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ይዘው ይጀምሩ እንጂ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ መቆየትን የመረጡት ሀዋሳዎች ከሚያቋርጧቸው ኳሶች በመነሳት አስፈሪ ሆነው ታይተዋል። 4ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን ጥቃት ብሩክ በየነ ያሳለፈው ኳስም በመስፍን ታፈሰ አማካይነት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ መሆን ቢችልም አቤል ማሞ አድኖታል።

በሂደት የሀዋሳን ጫና በቅብብሎች እያለፉ ወደ ግብ መቅረብ የጀመሩት ቡናዎችም 10ኛው ደቂቃ ላይ አቤል እንዳለ በቀኝ ከዊሊያም ሰለሞን ተቀብሎ በሞከረው እና ለጥቂት በጎን በወጣው ኳስ ምላሽ ሰጥተዋል። ሀዋሳዎችም መስፍን በተሰለፈበት የግራ መስመር ቀጥተኛ በሆነ አጨዋወት ወደ ግብ ሲደርሱ ታይተዋል። በተለይ 19ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን በድጋሚ ከብሩክ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ የመቀየር ዕድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ቀጣዮቹ ደቂቃዎች እንቅስቃሴው መሀል ሜዳ ላይ ያመዘነባቸው ነበሩ። ይልቁኑም ከውሀ ዕረፍቱ መልስ ሀዋሳዎች በበቃሉ ገነነ ፣ ብሩክ በየነ እና መስፍን ታፈሰ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የውሳኔ አሳጣጣቸው ግብ ከማስቆጠር ገትቷቸዋል። በቀሩት የአጋማሹ ደቂቃዎች ቡናዎች ከኳስ ጋር ብዙ በመቆየት ክፍተቶችን ለማግኘት ሲሞክሩ ሀዋሳዎች በበኩላቸው ይህ እንዳይሆን በቁጥር በርክተው በጥንቃቄ ከራሳቸው ሜዳ እምብዛም ሳይርቁ ተጫውተው አጋማሹ ሌላ ጠንካራ የግብ ሙከራ ሳይታይበት ተጠናቋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ እንደቀደመው ሁሉ ኳሶችን ወደ ፊት መጣልን ምርጫቸው ያደረጉት ሀዋሳዎች በተመሳሳይ አኳኋን ሳጥን ውስጥ ደረሰው ቴዎድሮስ በቀለ ወንድምአገኝ ኃይሉ ላይ በሰራው ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። 49ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ አጋጣሚውን ግብ አድርጎታል። ከግቡም በኋላ ሀዋሳዎች የቡናን ኳስ ፍሰት በመቆጣጠር እና ፈጥኖ ወደ ፊት በመሄድ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። በተለይም 60ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ከቀኝ አሻግሮለት ብሩክ ከቅርብ ርቀት ያደረገው ሙከራ በአቤል ማሞ ጥረት የዳነ ነበር። ሆኖም ከአንድ ደቂቃ በኋላ መሀል ላይ ከአብዱልባስጥ ከማል ተነስቶ ከቡና ተከላካዮች ጀርባ የደረሰውን ኳስ መስፍን ታፈሰ በአቤል መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ግብ ለማስቆጠር በሚያደርጉት ጥረት በሀዋሳ ሜዳ ላይ እንደልብ ክፍተት ማግኘት ሳይችሉ ቆይተዋል። ከሁለተኛው ውሀ ዕረፍት በፊት የአጋማሹን ጥሩ ሙከራ ሲያደርጉ ስዩም ተስፋዬ ከቅጣት ምት በተነሳ እና ሀዋሳዎች ለማራቅ የሞከሩትን ኳስ በመያዝ ተጫዋቾችን አልፎ ግብ አፋፍ በመድረስ ያደረገው ሙከራ ግብ ለመሆን ተቃርቦ ነበር። ከዕረፍቱ መልስም እንዲሁ የአዲስዓለም ደበበን የቅብብል ስህተት ተጠቅመው ወደ ሳጥን ቢደርሱም የታፈሰ ሰለሞን ጥረት በመሀመድ ሙንታሪ ድኗል።


የቡና ጫና እና ሙከራዎች ቀዝቅዝ ባሉባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች ሀዋሳዎች በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ይጥሩ ነበር። በተለይም ብሩክን ቀይሮ የገባው ተባረክ ሄፋሞ 86ኛው ደቂቃ ላይ ከአቤል ማሞ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘበትን አጋጣሚ አባከነ እንጂ ሦስተኛ ግብ ሊቆጠር ተቃርቦ ነበር። በቀሩት ደቂቃዎችም የቡና የኳስ ቁጥጥር ቀጥሎ ቢታይም ቡድኑ ውጤት ማጥበብ የሚችልበትን ግብ ሳያገኝ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።


ውጤቱን የከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 17 በማድረስ ከመሪው ፋሲል ከነማ በአንድ አንሶ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ በግብ ልዩነት ተበልጦ ሦስተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል።

ያጋሩ