​የከፍተኛ ሊጉ አንደኛ ዙር ግምገማ ተካሂዷል

የፌዴሬሽን እና የክለብ አመራሮች የተገኙበት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ግምገማ ዛሬ ተከናውኗል።

ከ03:00 ጀምሮ በጁፒተር ሆቴል የተካሄደው የከፍተኛ ሊጉ የአንደኛ ዙር ግምገማ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የመክፈቻ ንግግር ተጀምሯል። አቶ ኢሳይያስ ከብሔዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ጋር አያይዘው የከፍተኛ ሊጉ ክለቦች አመራሮች ውይይታቸው ሊጉ ሊኖረው ከሚገባው ሀገራዊ ግብዓት አንፃር እንዲቃኝ አሳስበዋል። 

በመቀጠል በሦስት ምድቦች ተከፍሎ ሲካሄድ የነበረውን ውድድር አስመልክቶ አቶ ኃይሉ ምህረትአየሁ ፣ አቶ ሰለሞን እንዳለ እና አቶ ዳዊት አሰፋ የየምድቦቹን ሪፖርቶች አቅርበዋል።በሪፖርታቸውም የታዩ ችግሮች እና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በዝርዝር ሲቀርቡ የኮቪድ ፕሮቶሎኮል ፣ የዳኝነት እና የሜዳ ጉዳዮች አመዛኙን ሽፋን አግኝተዋል።

ግምገማው ከሻይ ዕረፍት መልስ ሲቀጥል የተሳታፊ ክለቦች ተወካዮች የተለያዩ ሀሳቦችን አንሸራሽረው ጥያቄዎችንም አቅርበዋል። በውድድሩ የአንደኛ ዙር ጨዋታዎች ሂደት ወቅት ክለቦች የገጠሟቸውን ችግሮች ያብራሩ ሲሆን በአመዛኞቹ ተሳታፊዎች ጠቅለል በለው የተሰጡ ሀሳቦችም ነበሩ። በዋነኝነት ከተነሱ ነጥቦች መካከል የዳኞች የአካል ብቃት እና የብቃት ችግር ላይ መሰራት እንዳለበት ፣ የመጫወቻ እና የልምምድ ሜዳዎች ጉዳይ ፣ በጨዋታዎች መርሐ ግብሮች መሀል ያለ የዕረፍት ማጠር ፣ ግምገማዎች ከተለመደው አካሄድ ውጪ ቴክኒካዊ ዕይታዎች እንዲኖራቸው መሰራት እንዳለበት ፣ ከውድድሩ ደንብ ውጪ በጨዋታዎች ላይ ደጋፊዎች በብዛት ስለመታደማቸው ይገኙበታል።

በመቀጠል ከመድረኩ በተነሱ ሀሳቦች ላይ የኮሚቴ አመራሮች ምላሽ ሰጥተዋል። በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ልዑል በግምገማው ላይ በዳኞች ዙሪያ ለተነሱ ሀሳቦች ምላሽ ሲሰጡ የዳኞች ብቃት ችግር መኖሩን አምነው በምደባ እና በብቃት ማሻሻያ ላይ እንደሚሰሩ በዝርዝር አንስተዋል። በሌሎች የኮሚቴ አባላት በተነሱ ሀሳቦችም 

በአንድ ጨዋታ አምስት ተጫዋቾችን እስከ ሦስት አጋጣሚዎች ድረስ መቀየር  እንደሚቻል ፣ የሰላም ሚኒስትር በፈቀደው መሰረት 25 በመቶው ደጋፊዎች እንዲገቡ መፈቀዱ ፣ ዳኞች ስህተት ቀንሰው እንዲሰሩ የተሻሉ ዳኞችን ለመመደብ ጥረት እንደሚደረግ ፣ በውድድሩ ደንብ ላይ ያልተካተቱ ጉዳዮችን ኮሚቴው በድጋሚ በማየት ለክለቦች እንሰሚበተኑ እንዱሁም የውድድርም ሆነ የልምምድ ሜዳ እንደሀገር ያለ ችግር በመሆኑ ወደፊትም በቶሎ የማይቀረፍ ችግር መሆኑ ተነስቷል።

በመቀጠል የጉባዓውን ግልፅነት በማድነቅ የጀመሩት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የዳኞችን አቅም ለማሻሻል ሥራዎች እየሰሩ እንደሚቀጥሉ ሆኖም ሆን ብለው ስህተት የሚሰሩ ዳኞች ጉዳይ ሌብነት በመሆኑ መታገስ እንደማይገባ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን የቡድን መሪዎችም በጨዋታ ወቅት በዳኞች ላይ የሚያሳዩትን ባህሪም ኮንነዋል። ፕሬዝዳንቱ የሜዳ ችግር ሀገራዊ መሆኑን አንስተው ክለቦችም ችግሩን ከራሳቸው የሜዳ ዝግጁነት አንፃር ማየት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ በኮቪድ ምርመራ ፣ በጨዋታ ቀናት መሀል ባለው ክፍተት ላይ ኮሚቴዎች ከክለቦች የፋይናንስ አቅም አንፃር እንዲመለከቱት እንዲሁም በውድድር ቅፆች ላይ የሚመለከቷቸው ኮሚቴዎች ከክለቦች ጋር አብረው እንዲሰሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ ሁለተኛው ዙር የከፍተኛ ሊግ ውድድር ምድብ አንድ በባህርዳር ፣ ምድብ ሁለት በባቱ ፣ ምድብ ሦስት ደግሞ በሀዋሳ እንደሚካሄዱ ተገልጿል። በመጨረሻም ክለቦች ለመከላከያ እና ለተፈናቀሉ ወገኖች ቃል የተገባውን የገንዘብ ድጋፍ በአግባቡ እንዲፈፅሙ መልዕክት ተላልፎ ግምገማው ተፈፅሟል።