​ሪፖርት | ድንቅ ምሽት ያሳለፉት ፈረሰኞቹ መሪነቱን ተቆናጠዋል

በ10ኛው ሳምንት ተጠባቂ በነበረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፋሲል ከነማን ከጨዋታ ብልጫ ጋር 4-0 መርታት ችሏል።

የጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር ከመጀመሪያው ደቂቃ የጀመረ ነበር። ፋሲል ከነማዎች ወደ ሳጥን ባደረሷቸው ኳሶች እና በጊዮርጊሱ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ የ2ኛ ደቂቃ የርቀት ሙከራ የጨዋታው ግለት ከፍ ያለ መሆኑ ታይቷል። ከሚቋረጡ ኳሶች በቶሎ ወደ ግብ መድረስን ዓላማቸው ያደረጉት የጊዮርጊሶች መልሶ ማጥቃት አስፈሪነቱ እየጎላ ቆይቶም ወደ ግብነት ተቀይሯል። 10ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከራሳቸው ሜዳ በተነሳ መልሶ ማጥቃት በአማኑኤል ገብረሚካኤል አመቻችነት እና በአቤል ያለው አስቆጣሪነት ጨዋታውን በጊዜ መምራት ችለዋል።

ከግቡ በኋላም ጊዮርጊስ ፈጣን ጥቃት የተሻለ አስፈሪነት ሲታይበት ፋሲሎች ኳስ ይዘው ክፍተቶችን ለማግኘት የሚሞክሩበት መንገድ በተቃራኒው ለተጋጣሚያቸው የጨዋታ ዕቅድ ሲያጋልጣቸው ታይቷል። ቡድኑ 21ኛው ደቂቃ ላይ ከሱራፌል ዳኛቸው ቅጣት ምት ያደረገው የቅጣት ምት ሙከራ ብቻ የተሻለው የአጋማሹ ሙከራው ነበር።

ከውሀ ዕረፍቱ በኋላም ጨዋታው በተመሳሳይ አኳኋን ቀጥሏል። ሆኖም የፉክክር መጠኑ እየጨመረ መሄድ ጉልበት እየበዛበት እንዲሄድ እና በቀሪ ደቂቃዎች አምስት ቢጫ ካርዶች እንዲመዘዙ አድርጓል። በእንቅስቃሴም የፋሲል ከነማ የኳስ ምስረታ ሙከራ የጊዮርጊስ ማጨናገፍ እና ወደ ግብ በፍጥነት መድረስ ተደጋግሞ መታየት ቀጥሏል። 

36ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር አጥቂነት የተሰየመው አቤል ያለው ወደ ሳጥን የላካው የመልሶ ማጥቃት ኳስ በተከላካዮች ሲጨረፍ ከነዓን ማርክነህ ወደ ግብ ሞክሮ ሚኬል ሳማኬ አድኖበታል። ሆኖም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ጊዮርጊሶች ጋቶች ፓኖም መሀል ላይ በነጠቀው እና በቀኝ አቅጣጫ የሰነጠቀውን ኳስ አቤል ይዞ በመግባት በጥሩ አጨራረስ ግብ አድርጎታል። የጨዋታ ዕቅዳቸው የሚፈልጉትን ግብ ያልመታላቸው ፋሲሎች የግብ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ጊዮርጊስን የሚፈትኑ ዕድሎችን ሳያገኙ አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ፋሲሎች የጨዋታ ፍጥነታቸውን ጨምረው ጫን በማለት ጀምረዋል። በ52ኛው ደቂቃ ዓለምብርሀን ከቀኝ መስመር ካሻማውን ኳስ ኦኪኪ አፎላቢ  ያደረገው መከራም በዚህ ውስጥ ይጠቀሳል። ለጫናው በቀላሉ ክፍተት ባለመስጠት የቀጠሉት ጊዮርጊሶች ግን ውጤቱን ይበልጥ ማስፋት የሚችሉባቸው ዕድሎች በተከታታይ ፈጥረዋል። 57ኛው ደቂቃ ላይ  ከነዓን ማርክነህ የአስቻለው ታመነን ስህተት ተከትሎ ያገኘውን ግልፅ የማግባት ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከደቂቃ በኋላም በረጅሙ የተላከን ኳስ አስቻለው ጨርፎት አማኑኤል ንፁህ የግብ ዕድል ቢፈጥርም የአጎሮ ደካማ አጨራረስ በያሬድ እንዲመለስ አድርጓል።

ይሁን እንጂ ሌላኛውን የፋሲል ተከላካዮች ስህተት ጊዮርጊሶች አላሳለፉትም። አማኑኤልን ቀይቶ የገባው ቸርነት ጉግሳ በረጅሙ ከፋሲል ተከላካዮች ጀርባ የተጣለውን ኳስ ይዞ በመግባት ያደረገው ሙከራ በግቡ ቋሚ ሲመለስ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ደርሶ 62ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛ ግብ አስቆጥሯል።

ከግብ ልዩነቱ መስፋት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሜዳቸው ቀረት ብለው ጨዋታውን ማቀዝቀዝን መርጠዋል። ሆኖም 73ኛው ደቂቃ ላይ የአብስራ ተስፋዬ የሳማኬን መውጣት ተመልክቶ ከመሀል ሜዳ ያደረገው ለግብ የቀረበ ሙከራ ሙሉ ለሙሉ አለማፈግፈጋቸውን ያሳየ ነበር። የቻምፒዮኖቹ የኳስ ቁጥጥር እና የማጥቃት ጥረቶች ግን አሁንም ፈረሰኞቹን ማስከፈት ሳይችል ቀርቷል።

ይልቁኑም ጊዮርጊሶች በሌላ ፈጣን ጥቃት 88ኛው ደቂቃ ላይ በአጎሮ አራተኛ ግብ ለማስቆጠር ቢቃረቡም በግቡ ቋሙ ተመልሷባቸዋል። ፋሲሎችም በተመሳሳይ 90ኛው ደቂቃ ላይ በሱራፌል የቅጣት ምት ኳስ ያደረጉት ሙከራ በግቡ አግዳሚ የዳነ ነበር። ተጫዋቹ ከአንድ ደቂቃ በኋላም ከርቀት ሌላ ኳስ አክርሮ ሞክሮ በቻርለስ ሉኩዋጎ ተመልሶበታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩ ግን ሌላ የፋሲሎችን ስህተት በመጠቀም አጎሮ አራተኛ ግብ አክሎ በግለት የጀመረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን የ4-0 ባለድል አድርጎ በግለት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሁለተኛ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 20 አድርሶ ፋሲል ከነማን በሁለት በመብለጥ አንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።