​የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-0 ፋሲል ከነማ

የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ አገናኝቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት አጋርተዋል።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው

በአፍሪካ ዋንጫ አንድ ወር ዕረፍት ነበር። በዚሁ አጋጣሚ መስራት ያለብን መሆን ስለሚገባን ነገር ሰርተን ነበር። ያንን ነገር ልጆቼ አሳክተውልኝ ጥሩ ውጤት ይዘውልኝ ወጥተዋል።

የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት

አጥበን በመጫወት እነርሱ ኳሱን ይዘው ሊጫወቱ ይችላሉ። ይህን ኳስ ቀምተን ወደ መልሶ ማጥቃት ሽግግር መግባት ፈልገን ነበር። ያልኳቸውን ነገር ተግብረውልኛል ፤ በልጆቼ ደስተኛ ነኝ።

ጊዮርጊስ መሪነቱን ስለመረከቡ

እኛ ከፊት ከፊት ያሉትን ጨዋታዎች እያሸነፍን ወደ ፊት መሄድ ነው የምንፈልገው። ሌላ ነገር አንፈልግም። በድሬደዋ ቆይታችን የመጀመርያውን ጨዋታ አሸንፈናል ሁሉንም ከፈጣሪ ጋር እየሰራን ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ነው የምንሰራው።
በቀጣይ የቡድኑ አጨዋወት በዚህ መልኩ

ስለመቀጠሉ

ይህ ጨዋታ ትልቅ ጨዋታ ነው። በእኛ ሀገር ሊግ የአቋም መዋዥቅ አለ። ግን እኔ የዛሬውን ጨዋታ ተከታታይነት ባለው ከዚህ የተሻለ ነገር ሰርተን የተሻለ ውጤት ለማምጣት ነው የምናስበው።

ስለደስታ አገላለፃቸው
ምንም ዓይነት ጭንቀት አልነበረብኝም። ጎል ሲገባ ተጫዋች ስለነበርኩ እና ስሜቱን ስለማውቀው ያ ስሜት ነው። ልጆቼ የነገርኳቸውን ነገሮች ስላደረጉልኝ ደስተኛ በመሆኔ ነው።

ዋና አሰልጣኝ ስለመሆን

ማንም ሰው ይመኛል ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስን የማይመኘው የለም። ግን ዋናው ስራው እና ስራው ነው የሚወስነው። እኔ የተሰጠኝን ኃላፊነት ስራ አክብሬ መስራት ነው የምፈልገው

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው

በአጠቃላይ ጨዋታው ባሰብነው መልኩ አይደለም የሄደልን። እስካሁን ዘጠኝ ጨዋታዎች አድርገናል ይህ አስረኛችን ነው። በዛሬው ጨዋታ ሁሉም ተጫዋቾች ተገኝተዋል ፤ ከሀብታሙ ተከስተ በቀር። ግን የነበረን አጀማመር እና ተነሳሽነት እነርሱ የተሻሉ ነበር። በተለይ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ፈጣን ነበር። እኛ ደግሞ ይህን ቦታ ፈቅደንላቸዋል። የምናልመው ጎል ማስቆጠር ላይ ብቻ ነበር። ሌሎች ክፍተቶቻችን ላይ ዞር ብለን አላየንም። ሁለቱ ጎሎች የእነሱን የመጫወት መንፈስ ከፍ ሲያደርግ በተቃራኒው እኛ ባቀድነው ልክ የመጀመርያው አጋማሽ አልሄደም። ከዕረፍት መልስ የተወሰነ ሞክረናል። አስራ ስድስት ከሀምሳ ውስጥ ጎል የመፈለግ አካሄዳችን በብዙ መልክ መስተካከል ያለበት መሆኑን አይተናል። ይህ አስረኛው ጨዋታችን ከሌሎች ጨዋታዎች በተለየ በብዙ ቦታዎች ላይ የተበላሹ ነገሮች አሉ። ለዚህም የገቡት ጎሎች የሚናገሩት ነገሮች አሉ። በቀጣይ ጨዋታዎች አስተካክለን ከፍ ለማለት እንሞክራለን።

በመጀመርያው አጋማሽ የነበረውን ክፍተት በቀጣይ አለማረማቸው

ለማድረግ ፈልገን የነበረው በነእርሱ ሜዳ ገብተን የተበላሹ ነገሮችን በመፈለግ አንድ ጎል በማስቆጠር የቡድኑን ስሜት ለማነሳሳት እና እነዛን ቀዳዳዎች ለማግኘት የነበረን መቀናጀት ከኋላ መስመር መሐል ላይ ካሉት ተደምረው ወደ ውስጥ የመግባት ነገራችን በብዙ መልክ ስህተት ነበረበት። እንደዛም ሆኖ ከኋላ ያሉት አማካዮቹ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የሚሰጡት ክፍተት የበዛ ነበር። እንደፈለጉ እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል። ሰው በሰው አጨዋወታችን ጥሩ አይደለም። ቦታ አበላሽተናል። እነዚህ ነገሮች የበለጠ ክፍተት ፈጥረዋል ብዬ አስባለው።

ከአፍሪካ ዋንጫ ስለተመለሱ የቡድኑ ተጫዋቾች

በሌሎች ቡድኖች የነበሩ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ቡድናቸውን እያገለገሉ ነው። ከብሔራዊ ቡድን እንደተመለሱ በቀጥታ ወደ ልምምድ አላስገባናቸውም። አራት ቀን ዕረፍት ሰጥተናል። ጥሩ ሽግግር አግኝተዋል ብዬ ነው የማስበው። ነገር ግን ከጅምሩ አብረን በነበረው የልምምድ ዘርፎች ሁሉ  ጥሩ መነቃቃት ጥሩ ስሜት አላቸው ። ነገር ግን ሜዳ ላይ ቀድመው እነዛ የሚፈለገውን ነገር መውሰዳቸው የእኛን ስሜት አውርደውታል።