ፌዴሬሽኑ በዑመድ ኡኩሪ ዙርያ ምላሽ ሰጥቷል

👉 “…በሁለተኛ ደብዳቤ አሰልጣኞቹ ዑመድን ጨምሮ የሚሄዱትን ስም ዝርዝር ልከናል።

👉 “ለምድነው በዚህ ጉዳይ የዑመድ ጉዳይ መነሻ የሆነው? ሊዮኔል ሜሲ ነው እንዴ? አልገባኝም።

👉 “ከዚህ ቀደም ለብሔራዊ ቡድን ለሰራቸው ላበረከታቸው ነገሮች ክብር አለን።

👉 “እንዳውም የሌላ ወጣት ቦታ ተይዞብናል ብለን ነው የምናምነው።


👉 “በአሜሪካ ጉዞ ባነሳው ነገር ተጠያቂ የምንሆንበት ምንም ምክንያት የለም።

ሶከር ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ዑመድ ኡኩሪ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ለማግለል ምክንያት ስለሆነው ጉዳይ በሰፊው የሰጠውን ማብራሪያ ማቅረባችን ይታወቃል። ዛሬ ደግሞ ከአሜሪካ የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጉዞን አስመልክቶ በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ በዑመድ ኡኩሪ ዙርያ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ባህሩ ጥላሁን ምላሽ ሰጥተዋል። ዋና ሥራ አስፈፃሚው የሰጡትን ምላሽ እንዲህ አቅርበነዋል።

“ጥያቄው መሆን ያለበት ‘ዑመድ ለምን ተመረጠ ነው ወይስ ለምን መሄድ አለበት ?’ ነው። አሁን ባለበት ሁኔታ ዑመድ ለብሔራዊ ቡድን ይመጥናል ወይ የሚለውን ጥያቄ ለእናንተ ልተውው ፤ ዑመድ ለበርካታ ዓመታት ለብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ያየሁበት ጊዜ የለም። ለመጨረሻ ጊዜ የተመረጠው የጊኒ ጨዋታ ወቅት ነው። በወቅቱ በጊኒ ጨዋታ ወቅት የተሳተፉት ወደ አሜሪካ እንዲሄዱ ፕሮሰስ እንዲደረግ አስተዳደሩ የወሰነላቸው ቡድኑ አሰልጣኝ አልባ በመሆኑ ለብሔራዊ ቡድን ምርጫ ማነው የሚያካሄደው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ወይስ ፕሬዝደንቱ ? ይህን ለማድረግ እንቸገራለን። ስለዚህ ውሳኔ የተሰጠው የጊኒው ስብስብ እንዲሄድ ነው። በመቀጠል መሞላት ያለባቸው የፎርም ጉዳዮች እንዲከናወኑ ተደርጓል።

“በዚህ ሂደት የዑመድ ፎርም ሳይሞላ ቀርቶ ባለበት ዑመድ ደውሎ ወደ ሀገር ቤት መመለሱን ነግሮኝ እኔ ነኝ የጠየኩት። ‘የአሜሪካው ጉዞ ፎርም ተሞላ አልኩት ?’ ‘ኧረ ምንም ነገር የለም’ አለኝ። ወድያውኑ ፎርሙ እንዲሞላ ሆነ። በተመሳሳይም የእነ ሱራፌል የሌሎችም ተጫዋቾች ፎርም እንዲሞላ ተደርጓል። ፌዴሬሽኑ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲያደርግልን በላከውን የመጀመርያው ስም ዝርዝር ዑመድን ጨምሮ የአሰልጣኝ አባላት እና የተወሰኑ ተጫዋቾች ስም አልተላከም። በሁለተኛ ደብዳቤ ደግሞ አሰልጣኞቹ ዑመድን ጨምሮ የሚሄዱትን ስም ዝርዝር ልከናል። የዑመድ ስም በአረባ ሁለተኛ ላይ ተፅፏል። ለእያንዳንዱ ነገር ፌዴሬሽኑ ግልፅ መረጃ አለው።

በዚህ ሂደት ክፍተቱ ምንድነው ቀጠሮ በሚያዝበት ወቅት የአሜሪካ ኤንባሲ አሰራር ይታወቃል ዑመድ በአስቸኳይ ቀጠሮ የሚያገኝበትን መንገድ እንዲያመቻች ነገርነው ፤ ፌዴሬሽኑ ቀጠሮ የማፍጠን ስልጣን ስሌለው። ቀጠሮ አሳጥሮ እንዲገባ ተነገረው ሌሎችም በዚህ መልክ አሳጥረው የገቡ ስላሉ በዚህ መልኩ እንዲያደርግ ተነገረው። በአጋጣሚም ቀጠሮ ተገኘለት። በዚህ ሁኔታ ኢንስትራክተር ዳንኤል ለእኛ ምን አቀረበ ‘ዑመድ ምን ሊሰራልኝ ነው የጠራችሁት ? ወቅታዊ አቋሙን እኔ አይቼው አላውቅም በየትኛው መንገድ ነው የተጠራው ?’ ቢልም አይ የተጠራው ቃል በተገባው መሰረት ነው በማለት አሰልጣኙን ተጭነነዋል። እንዳውም ቪዛው ካልተሰጠኝ ዝግጅት አልገባም ብሎ ነበር ።

“ሶከር ኢትዮጵያ ላይ የተፃፈውን አንብቤለው ክፈል የተባለው ክፍያ የቱ ነው ? ፌዴሬሽኑ ገንዘብ ለማውጣት የራሱ አሰራር አለው። ይህ አጣዳፊ ነው ክፈል እና ተመላሽ ይደረግልሀል ተባለ ፤ በዚህ መሰረት ከፍሎ ገባ ቪዛው ተሰጠው። የአስቸኳይ ሲሆን ቢጫው ይሰጣል እርሱ ነጭ ተቀበለ። አሰልጣኙም ሌሎች ተጫዋቾች ነጩን ነበር የተቀበሉት ግን ሄደው ቢጫውን ወስደዋል። የእርሱ ግን ነጭ ሆነ የፕሮቶኮል ክፍሉ ለምን ነጭ ተቀበልክ ቪዛው ይረዝምብሀል ተባለ። በዚህ ሂደት ቪዛውን የሚቀበለው ሰኞ ሆነ ፌዴሬሽኑ ደግሞ እሁድ ሊሄድ ትኬት ቆርጦ ጨርሷል። የመጫወቻ ማሊያ ታትሟል ፤ የዑመድን ጨምሮ ይህው ማሳየት ይቻላል። አስራ አንድ ቁጥር ማልያ ተዘጋጅቶለታል። ምን ብለን ነው ልናስቀረው የምንችለው ?

“ከዚህ በኋላ እኛ እዛ ደረስን እርሱ ከማንም ጋር አልተገናኘም እንዳትመጣ ያለውም አካል የለም። እኛ በፕሮግራማችን መሰረት ጨዋታችንን አድርገን መጥተናል። እንዳውም የሌላ ወጣት ቦታ ተይዞብናል ብለን ነው የምናምነው። በዚህ ምክንያት ራሴን ከብሔራዊ ቡድን አግልያለው የሚለው ነገር የምቀበለው አይደለም። ከዚህ ቀደም ለብሔራዊ ቡድን ለሰራቸው ላበረከታቸው ነገሮች ክብር አለን። በአሜሪካ ጉዞ ባነሳው ነገር ግን ተጠያቂ የምንሆንበት ምንም ምክንያት የለም። እርሱ ቀርቶ ሌላ እንዲሄድ የተደረገበት አግባብ የለም።

“ለምድነው በዚህ ጉዳይ የዑመድ ጉዳይ መነሻ የሆነው? ሊዮኔል ሜሲ ነው እንዴ? አልገባኝም። ሲጀመር ወቅታዊ አቋሙን አናቅም እንዴ ? እኛን ግንኙነት አላደረግ በራስህም ቆርጠህ ና ያለው ማንም የለም። በዚህ ደረጃም ያዋራው የለም። ቪዛውን ሰኞ ይቀበል ማክሰኞ ይቀበል የምናቀው ነገር የለም። ቅንነትም ካለ ቆርጦ ቢመጣ አወራርዱልኝ ቢል ምን አለበት። ይህ ፌዴሬሽን አናወራርድም በጉልበትህ ነው የመጣህው የሚል ፌዴሬሽን አይደለም። በአጠቃላይ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ለማግለል ፌዴሬሽኑን ምክንያት ማቅረብ ተገቢ አይደለም።”