​ቅድመ ዳሰሳ | የ10ኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን ጨዋታዎች

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ሲቀጥል የሚደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች አስመልክቶ ተከታዮቹን መረጃዎች አንስተናል።

ጅማ አባ ጅፋር ከ አዲስ አበባ ከተማ

የነገው የመጀመሪያ ጨዋታ በውጤት እጦት ውስጥ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋርን እና ከአስገራሚ ግስጋሴው የተቀዛቀዘው አዲስ አበባን ያገናኛል።

እስካሁን አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት አባ ጅፋሮች የሀዋሳ ቆይታቸውን መጥፎ ትዝታ ድሬዳዋ ላይ በመርሳት በፍጥነት ወደ ውጤት መመለስ ያስፈልጋቸዋል።  አዲስ አበባዎችም ቢሆኑ በተከታታይ ድሎች በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ላይ ከፍ ማለት ጀምረው የነበሩትን መንገድ መልሰው ለማግኘት ከዚህ ጨዋታ ካልጀመሩ ቀጣይ መንገዳቸው መክበዱ የሚቀር አይመስልም።

በሁለቱ ተጋጣሚዎቹ መካከል የነበረው የተጫዋች እያሱ ለገሰ ይገባኛል እሰጥ አገባ ጉዳይ በጅማ አባ ጅፋር አሸናፊነት በተጠናቀቀ ማግስት ጨዋታው መደረጉ ደግሞ ትኩረትን ይስባል። እያሱም በነገው ጨዋታ ላይ ጨዋታውን በተጠባባቂን እንደሚጀምር ተሰምቷል። በሁለቱም በኩል በጉዳት እና ቅጣት ሳቢያ ወደ ሜዳ የማይገባ ተጫዋች አለመኖሩንም ሰምተናል።

ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ በመሀል ዳኝነት ትንሳኤ ፈለቀ እና አብዱ ይጥናው በረዳትነት እንዲሁም ኃይለየሱስ ባዘዘው በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– አዲስ አበባ ከተማ 2009 ላይ ብቸኛ የሊጉ ተሳትፎውን አድርጎ ወደ ከፍተኛ ሊጊ ሲወርድ ጅማ አባ ጅፋር ዋንጫውን ባነሳበት የ2010 የውድድር ዓመት በመምጣቱ የነገው ጨዋታ የመጀመሪያ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ይሆናል።

ሰበታ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

በሊጉ ከጅማ አባ ጅፋር ብቻ በልጦ የተቀመጠው ሰበታ ከተማ ከአደጋ ዞኑ ለመውጣት አዳማ ከተማ ደግሞ ከሰንጠረዡ ወገብ ከፍ ማለትን አልመው ይፋለማሉ።

እስካሁን አንድ ድል ብቻ ያላቸው ሰበታ ከተማዎች በክረምቱ የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የዝግጅት ውድድር ላይ ያሳዩን ብቃት ርቋቸው ይገኛል። በተለይም በሀዋሳ ቆይታቸው 12 ግቦችን ማስተናገዳቸው ላሉበት ዝቅተኛ ደረጃ ምክንያት ይሆነ ይመስላል። በተቃራኒው አንድ ጨዋታ ብቻ የተሸነፉት አዳማ ከተማዎች ደግሞ አመዛኙን ጨዋታዎቻቸውን በጥሩ ብቃት ቢከውኑም የአቻ ውጤቶችን ማበርከታቸው ወደ ፉክክሩ እንዳይጠጉ አድርጓቸዋል።

በጨዋታው ሰበታ ከተማ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች የለም። አዳማ ከተማዎችም ኮንትራታቸው አልቆ በድርድር ላይ ከሚገኙት አሚን ነስሩ እና ኤልያስ ማሞ በቀር ሙሉ ስንስቡ ለጨዋታው ዝግጁ ነው።

የጨዋታው የመሀል ዳኝነት በፌደራል ዳኛ ሄኖክ አክሊሉ ሲከወን ረዳት ዳኞቹ ተመስገን ሳሙኤል እና ፍሬዝጊ ተስፋዬ እንዲሁም አራተኛ ዳኛው ሚካኤል ጣዕመ ይሆናሉ።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ ተመጣጣኝ የግንኙነት ታሪክ አላቸው። እስካሁን በተገናኙባቸው ስምንት ጨዋታዎች ሦስት ሦስት ጊዜ ሲሸናነፉ  በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ዝቅተኛ የግብ መጠን በሚያስተናግደው ግንኙነታቸው ሁለቱም አራት አራት ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል።