​ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከመመራት ተነስቶ አሸንፏል

አመሻሽ ላይ በተደረገው ጨዋታ አዳማ ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ሰበታ ከተማን በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል።

እንደ አየር ንብረቱ ሁሉ ቀዝቃዛ መልክ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ መሀል ሜዳ ላይ የተጫቀ እንቅስቃሴ የበረከተበት ነገር ግን ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎች በብዛት ያልነበሩበት ነበር።

የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው አዳማ ከተማዎች ከኳስ ውጪ ከፊት አጥቂያቸው ዘካርያስ ፍቅሬ ሌላ በርከት ብለው ይከላከሉ የነበሩትን የሰበታ ተጫዋቾች የመከላከል ውቅርን ጥሶ ለመግባት በጣሙን የተቸገሩበት አጋማሽ ነበር ። በአንፃሩ ሰበታዎች በጥንቃቄ ከመከላከል ባለፈ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ከፍ ብለው የአዳማን የኳስ ቅብብሎች በማቋረጥ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

ጨዋታው ወደ ውሀ ዕረፍት ከማምራቱ በፊት የውጤት ለውጥ ተከስቷል ፤ በ23ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማው አማካይ ዮሴፍ ዮሀንስ በኳስ ምስረታ ሂደት ላይ ከተነጠቀው ኳስ መነሻነት የተገኘችውን የግብ ዕድል በሁለት አጋጣሚዎች ወደ ግብ ተሞክሮ ጀማል ጣሰው ካዳናቸው በኋላ በጨዋታው ከወትሮው በተለየ በመስመር አማካይነት ጨዋታውን የጀመረው ኃይለሚካኤል አደፍርስ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።


ከግቧ በኋላም ጨዋታው ተመሳሳይ ቀዝቃዛ ይዘት ነበረው። በ40ኛው ደቂቃ ኃይለሚካኤል በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ ያሻረውን ኳስ የጀማል ጣሰው እና ቶማስ ስምረቱ አለመግባባትን ተከትሎ ያገኘውን ኳስ ዘካርያስ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ለጥቂት ያመከናት ኳስ ሰበታዎች መሪነታቸውን ሊያሳድጉበት ይችሉበት ከነበረው አጋጣሚ ውጪ ተጠቃሽ አጋጣሚ ለመመልከት አልታደልንም።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ የማጥቃት ተነሳሽነት አክለው ብቅ ያሉት አዳማዎች አቻ ለመሆን አምስት ደቂቃ ብቻ ነበር የፈጀባቸው። የሰበታው ወልደአማኑኤል ጌቱ ኳስ ሳጥን ውስጥ በእጅ መንካቱን ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አምበላቸው ዳዋ ሆቴሳ አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መመለስ ችሏል።

የአዳማ ከተማዎች የማጥቃት ጨዋታቸው በፍጥነት የመቀዛቀዝ ምልክት ሲታይበት በአንፃሩ ሰበታዎች ከሚነጥቋቸው ኳሶች ግብ ለማግኘት ያደርጓቸው የነበሩ ጥረቶች አስፈሪ ይመስሉ ነበር።
በ73ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ናደው እና ዘካርያስ ፍቅሬ ከአዳማዎች የነጠቁትን ኳስ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል የፈጠሩትን አጋጣሚ ዘካርያስ ወደ ግብ ቢልክም ጀማል ጣሰው እና የቡድን አጋሮቹ ተረባርበው ሊያከሽፉበት ችለዋል። በተመሳሳይ በደቂቃዎች ልዩነት እንዲሁ ሳሙኤል ሳሊሶ ከሳጥን ጠርዝ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችሏል። ነገር ግን አዳማዎች በ79ኛው ደቂቃ ከደቂቃዎች በፊት አሜ መሀመድን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አብዲሳ ጀማል ያገኙትን ግሩም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ተረጋግቶ በማስቆጠር ዳግም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።


በተቀሩት ደቂቃዎች ሰበታዎች አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። 2-1 በሆነ ውጤት ጨዋታውን በበላይነት ማጠናቀቅ የቻሉት አዳማ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 15 በማሳደግ 5ኛ ደረጃ ሲቀመጡ ሰበታ ከተማ በነበረበት 7ነጥብ እና 15ኛ ደረጃ ላይ ረግቶ መቀመጥ ችሏል።

ያጋሩ