በምሽቱ ጨዋታ ሰበታ ከተማን ከአዳማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት አጋርተዋል።
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ሰበታ ከተማ
ስለ ጨዋታው
ጎል በማግባት ቀድመን ነበር። የጎል ዕድል በመፍጠርም ሂደቱም ጥሩ ነበር። ነገር ግን የመምራት ዕድሉን አልተጠቀምንም። አልፎም ደግሞ ተጨማሪ ጎል የማስቆጠር አቅማችን ደካማ ነበር።
ምክትል አሰልጣኞችን ባለመኖራቸው የተፈጠረ ጫና ስለመኖሩ
ምንም ጫና አልነበረውም ምክንያቱም ከተስፋ ቡድን ረዳት አሰልጣኞች መጥተው ነበር። በዚህ በኩል ምንም ዓይነት ጫና አልነበረውም።
በሁለተኛው አጋማሽ ስለተወሰደባቸው ብልጫ
ይሄ ይጠበቃል። ምክንያቱም አንድ ለምንም ነው እየመራን ያለነው ቡድናችን ከድል ርቋል። ይህን ውጤት ለማስጠበቅ ጉጉት ነበር። በዛ መነሻነት ወደ ኋላ አፈግፍገው እየተጫወቱ ነበር። ፍፁም ቅጣት ምቱ ሲቆጠር ወደ ፊት ሄደን ለመጫወት ጥረት አድርገናል። ከመራን በኋላ ጎል እስኪቆጠርብን ድረስ ውጤት ለማስጠበቅ ነው።
በቡድኑ ዙርያ መሰራት ስላለባቸው ጉዳይ
መሰራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ግድ ነው። አሸናፊ ብትሆንም መሰራት ያለባቸው ነገሮች ይኖራሉ። ነገር ግን የኛ ቡድን ዛሬ ምንም እንኳን ውጤት ማስጠበቅ ባይችልም ከወትሮ ከዚህ ቀደም ከነበረው እንቅስቃሴ ደህና ነበር። ግብ አጋጣሚዎች በመፍጠርም ቁጥሮች እንደሚናገረው ከወትሮ የተለየ ነገር እንዳለው ነው። አሁንም ጎል ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን የተገኙ አጋጣሚዎች ላይ አልተጠቀምንም። ከፊት መስመር ላይ የሰላ ነገር መኖር እንዳለበት ይሰማኛል።
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ
ስለቡድኑ የተለየ እንቅስቃሴ
በመጀመርያው አርባ አምስት እኛ በምናበላሻቸው ኳሶች እያጠቁን ነበር። በተጨማሪ በመጨወቻ የሜዳ ክፍል ላይ ትንሽ የፈጠራ እንቅስቃሴ አንሶን ነበር። ኳሶቻችን ትክክል አልነበሩም። በዛ ላይ ሰበታዎች በብዙ ቁጥር ሆነው ነበር የሚከላከሉት ስለዚህ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን በማስገባት እነርሱ ሜዳ ላይ በመብዛት ጎል ለማግባት ሞክረናል ሁለት ጎል በማግባት ተሳክቶልናል።
ስለ ውጤታማ ቅያሪ
እንዳልኩት ነው በመጀመርያው አርባ አምስት በብዙ ቁጥር በዝተው ይከላከሉ ነበር። የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ልጆች ቀይሮ በማስገባት እነርሱ የሜዳ ክፍል ላይ በመብዛት ጎል ለማስቆጠር ነው የሞከርነው። ያው በእግርኳስ የቀየርካቸው ተጫዋቾች ጎል ካስቆጠሩ ውጤታማ ነው ተብሎ ይወሰዳል። አንዳንድ ጊዜ ውጤታማ ሳይሆን ሲቀር ተቀይረው የገቡ ተጫዋቾች እንዳልተሳካ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። ከዕረፍት እንደመምጣታች ሦስት ነጥቡን ማግኘታችን ለእኛ ብዙ ነገራችን ነው።
ከመሪውዎቹ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት መቀራረብ
እንደሚታየው የሻምፒዮንነት ቦታው ክፍት ነው። ሁልጊዜም ወደ ላይ መመልከት ነው የምንፈልገው የመጨረሻውን ያለበትን ነጥብ ወይም የመሪውን ነጥብ በመደመር መሄድ አንፈልግም። በየጨዋታው የራሳችንን ዝግጅት እናደርጋለን። በየጨዋታው ሦስት ነጥብ ለማግኘት እንሞክራለን እንደዚህ እያደረግን ነው መሄድ የምንፈልገው።