የአሰረኛው ሳምንት ማሳረጊያ በሆኑት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ መከላከያ
ድሬዳዋ ከተማ በሀዋሳ ቆይታው እንደቅርብ ዓመታት ሁሉ በሰንጠረዡ የመጨረሻ ክፍል ላይ ሆኖ አጠናቋል። የመጨረሻ ጨዋታውን በድል መወጣት ቢችልም አጠቃላይ ውጤቱ ያላረካው በመሆኑ አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስን በማገድ ለአስረኛው ሳምንት የደረሰ ሲሆን ከአሰልጣኝ ፉዓድ የሱፍ ጋር በመቀመጫ ከተማው የሚደረጉትን ጨዋታዎች ያከናውናል። የድሬዳዋ ተጋጣሚ የሆነው መከላከያም እንዲሁ በአደጋው ዞን ውስጥ ነው የሚገኘው። ቡድኑ ከከፍተኛ ሊግ እንደመምጣቱ ሳይጠበቅ ጥሩ አጀማመር አድርጎ የነበረ ቢሆንም በሂደት ተዳክሞ የነጥብ ድምሩን ማሳደግ ተቸግሮ ሀዋሳን ተሰናብቷል። በመሆኑም ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች በቶሎ አንሰራርቶ ድሬዳዋ ላይ የተሻለ ውጤት ለመያዝ መነሻ ሊሆናቸው እንደሚችል ይጠበቃል።
በነገው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች ከሀገሩ ያልተመለሰው አዉዱ ናፊዩን ግልጋሎት የማያገኙ ሲሆን ጋዲሳ መብራቴ እና እንየው ካሳሁን መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል። በመከላከያ በኩል ያለው የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን ሳይሳካ ቀርቷል።
ጨዋታው በማኑኤ ወልደፃዲቅ ሲመራ ትግል ግዛው እና ሻረው ጌታቸው በረዳትነት አሸብር ጌታቸው ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበውበታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በእስካሁኑ የሊጉ ቆይታቸው 16 ጊዜ ተገናኝተዋል። ዘጠኙ በመከላከያ አሸናፊነት ሲጠናቀቁ አምስቴ አቻ ተለያይተው ድሬዳዋ ሁለት ጊዜ ብቻ ድል ቀንቶታል። በዚህም መከላከያ 26 ድሬዳዋ ከተማ 12 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
ወላይታ ድቻ ከ አርባምንጭ ከተማ
በሊጉ ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ ለቀጥተኛ አጨዋወት የሚያደሉት ድቻ እና አርባምንጭ የሚያደርጉት እና የዳንጉዛ ደርቢ በመባል የሚጠቀሰው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል። በመካከላቸው የሁለት ነጥብ ልዩነት ያለ ሲሆን ከበላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በሊጉ ግምት ሳይሰጠው የተሻለ አጀማመር ማድረግ ችሎ ነበር። የኋላ ኋላ አፈገፈገ እንጂ በላይኛው ፉክክር ውስጥ የተካተተበት እና ሊጉን የመራበት ጊዜም ነበር። አርባምንጮችም ከታች እንደመምጣታቸው ቀላል ግምት ቢሰጣቸውም በአንዳንድ ከባድ ጨዋታዎች ላይ ውጤት ይዘው በወጡባቸው አጋጣሚዎች ትኩረት መሳብ ችለው ነበር። ይሁን እንጂ ሁለቱም በቅ ጥልቅ ከሚል ጥሩ አቋም ውጪ በሊጉ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ የድሬዳዋ ቆያታቸውን እንዴት እንደሚጀመር ተጠባቂ ይሆናል።
የአርባምንጭ ሙሉ ስብስብ ለጨዋታው ብቁ መሆኑ ሲታወቅ የወላይታ ድቻን የቡድን ዜና ማግኘት አልቻልንም።
ይህንን ጨዋታ ለመምራት ዳንኤል ግርማይ በመሀል ዳኝነት ሲሰየሙ ይበቃል ደሳለኝ እና ክንፈ ይልማ ረዳት ዳኞች ለሚ ንጉሴ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ናቸው።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ከሁለቱ ቡድኖች የእስካሁኖቹ 10 ጨዋታዎች ስድስቱ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። ወላይታ ድቻ ሦስት ጊዜ ሲያሸንፍ አርባምንጭ ከተማ አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል። ግንኙነቱ ጥቂት ግቦች ሲቆጠሩበት ድቻ 6 አርባምንጭ ደግሞ 2 ጊዜ ብቻ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።