የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-0 መከላከያ

ድሬዳዋ ከተማ በጊዜያዊ አሰልጣኙ እየተመራ መከላከያን 1-0 ከረታ በኋላ ሁለቱም አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ፉአድ የሱፍ – የድሬዳዋ ጊዜያዊ አሰልጣኝ

ስለ ዕቅድ ትግበራ

“ሙሉ ለሙሉ እንኳን ተግባራዊ አላደረጉም ኳስ ይዘው እንዲጫወቱ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ግን ይታይ ነበር፡፡ ቀጣይ ላይ ይሄን አስተካክለን እንገባለን፡፡

ሜዳ ላይ ቢኒያም በላይ ላይ ትኩረት አድርገው ስለ መጫወታቸው

“አልነበረም። እኛ በግል ነው ሁሉም በአካባቢ ዞናል ማርኪንግ ነው የተጫወትነው እኛ የተለየ ተጫዋችን ያዙ ብለንም የሰጠነው አሳይመንት የለም፡፡

በጊዜያዊ አሰልጣኝ ቦታ ላይ ሆኖ ድል ስለ ማሳካታችው

“ለቀጣዩ በጣም ያዘጋጀናል ለእያንዳንዱ ያነሳሳናል፡፡ የሚያነሳሳ ውጤትም ስለሆነ ደስ ብሎናል፡፡”

አሰልጣኝ ዮሀንስ ሣህሌ – መከላከያ

ውጤት ስለማጣታቸው ምክንያት

“አለመጨረስ ነው። አልጨረስንም እንጂ ሌላው ደህና ነበርን፡፡ ኳሱን ወደ ፊት በመሄድ ባለጋራ ቡድን ውስጥ በመግባት ጥሩ ነበርን ግን አጨራረስ ላይ አልጨረስንም ብዬ ነው የማየው፡፡

በጉዳት ያልተሰለፉ ተጫዋቾች ስለመኖራቸው

“እሱ እንዳለ ሆኖ የገቡት ልጆች ስራቸውን መስራት አለባቸው፡፡ አስራ እንድ ልጆች ብቻ አይደለም መጫወት ያለበት። ሀያ ምናምን ተጫዋች ከያዝክ ዕድል ሲያገኝ እንደውም መጠቀም አለበት ብዬ ነው የምገምተው በእኔ ሀሳብ እና ያው የተሰጣቸውን ዕድል ያልተጠቀሙ አሉ። ግን አጠቃላይ ሁኔታው ስትመለከተው ከመጨረሱ በስተቀር ጥሩ ነው፡፡ ግን ኳስ ጨዋታ ነጥቡን ካልያዝከው ትርጉም የለውም፡፡

የዛሬው ውጤት በቀጣይ የድሬዳዋ ቆይታቸው ላይ ምን ይፈጥራል

“ገና ነው። በጨዋታ ደረጃ ከተመለከትከው ገና አንድ ሦስተኛ ነው የተጫወትነው ፤ ይሄ አስረኛ ጨዋታ ነው። ገና ሀያ ጨዋታ አለ ግን ደግሞ ያንን ማስተዛዘኛ ማድረግ የለብህም። እያንዳንዱ ጨዋታ እያንዳንዱ ጨዋታ ለውጥ ያመጣል፡፡”