ሪፖርት | ወላይታ ድቻ በደርቢው ጨዋታ ባለድል ሆኗል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ወላይታ ድቻ አርባምንጭ ከተማን በምንይሉ ወንድሙ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ማሸነፍ ችሏል።

ረጃጅም ኳሶች የበዙበት እንዲሁም ኃይል የቀላቀሉ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች እና የመከላካከል ስህተቶች የበረከቱበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ መመልከት ያልቻልንበት ነበር።

በንፅፅር አርባምንጭ ከተማዎች የተሻሉ በነበሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ ኤሪክ ካፓዬቶ እና ተካልኝ ደጀኔ በተሰለፉበት የግራ መስመር በኩል ተደጋጋሚ ቀጥተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በተደጋጋሚ ሲሞክሩ ተመልክተናል። በተቃራኒው በማጥቃቱ ረገድ ፍፁም ደካማ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ከቆሙ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ቢሞክሩም ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲጀመር በ47ኛው ደቂቃ የጨዋታው የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ተመዝግቧል። ከርቀት አርባምንጭ ከተማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ፀጋዬ አበራ አክርሮ ቢመታም ወንድወሰን አሸናፊ ሊያድንበት ችሏል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በንፅፅር የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው አርባምንጮች በኩል በ63ኛው ደቂቃ የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ወንድወሰን ከአንተነህ ጉግሳ የደረሰውን ኳስ ለማቀበል ብሎ የሰራውን ስህተት ተከትሎ ፀጋዬ አበራ ያገኘውን ወርቃማ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይጠቅምበት ቀርቷል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች አርባምንጮች የተሻሉ ቢመስሉም ወላይታ ድቻዎች አከታትለው ሁለት አደገኛ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በ67ኛው ደቂቃ ያሬድ ዳዊት በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን አጋጣሚ ይስሀቅ ሲያድንበት አስከትለው ካገኙት የማዕዘን ምት መነሻ ምንይሉ ወንድሙ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረው ኳስ የግቡ አግዳሚ ሊመልስበት ችሏል።

በ72ኛው ደቂቃ ግን ሀብታሙ ንጉሴ ከመሀል ሜዳ አካባቢ ለማሻማት ወደ ፊት የላከውን ኳስ የአርባምንጩ ግብ ጠባቂ ይስሀቅ ተገኝ ኳሱን በሚገባ መቆጣጠር ባለመቻሉ የተነሳ ዳግሞ ለመያዝ ባደረገው ጥረት ምንይሉ ወንድሙ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ምንይሉ አስቆጥሮ ቡድኑን ባለድል አድርጓል።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች በፍፁም መከላከል እና ጊዜ በማባከን ውጤቱን አስጠብቀው መውጣት ሲችሉ በአንፃሩ አርባምንጮች ይህ ነው የሚባል ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ድሉን ተከትሎ ድቻ በ16 ነጥብ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አርባምንጭ ከተማ በ11ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።