በአስረኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ወላይታ ድቻ አርባምንጭ ከተማን አንድ ለምንም ከረታ በኋላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት አካፍለዋል።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ
የጨዋታው መልክ ምን ይመስላል
“መጀመርያ ተናግሬያለሁ። በዕረፍት ወቅት እየተዘጋጀን ቆይተናል። አንደኛ በውይይት የሚጠናከሩ የተበላሸብን ነገሮች ስለነበሩ እነርሱን የማረም የማስተካከል ሥራዎችን ሰርተናል። ሁለተኛ በስልጠናው ስንዘጋጅ ሰንብተናል። በውድድሩ መጀመርያ ላይ የነበረው ታታሪነት ዛሬ መመልከት ችለናል። በእርግጥ በሁለታችንም በኩል ጠንካራ ፉክክር ነበር። በእርግጥ አርባምንጭ ቀላል የዋዛ ቡድን አይደለም። ጠንካራ ቡድን ነው። በሌላ በኩል የደርቢነት ስሜት ስለነበረው በታክቲክ የታጠረ ጥሩ እንቅስቃሴ የተደረገበት የማታ ጨዋታ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የአጨዋወት ስልታችንን ቀይረን ወደ ሜዳ ገብተን ወሳኝ ሦስት ነጥብ ስላገኘን ደስ ብሎኛል።
የጥንቃቄ አጨዋወት ስለመምረጣቸው
“ሊጉ እንደሚታየው እንደሌላው ዓመት አይደለም። ተያይዞ ነው እየሄደ ያለው መሪው ሃያ ነጥብ ነው ያለው። እኛ ደግሞ ዛሬ በማሸነፋችን አስራ ስድስት ነጥብ ገብተናል። ስለዚህ ከታች የነበሩ ቡድኖች እያሸነፉ ነው የመጡት እኛም በዚህ ልክ ነው መጓዝ ያለብን ምክንያት ከውድድር ከራቅን አንድ ወር ሆኖናል። የአካል ብቃታቸውን ለማምጣት እንደነዚህ ያሉ ቡድኖች ጋር ስትጫወት ጥንቃቄዎችን እያደረክ ጎል አስቆጥረህ የምትወጣበት መሆን ነው ያለበት። በራስ መተማመንህን ይዘህ ለሜዳው አዲስ ነን በሁለተኛው ጨዋታ እያሻሻልን እንመጣለን። እንደ ወላይታ ድቻ ሦስት ነጥብ በማግኘታችን ደስ ብሎኛል። ተጫዋቾቹ ያደረጉት ተጋድሎ ቀላል አይደለም። በዚህ አጋጣሚ ልጆቼን አመሰግናለው።
የስንታየው መንግስቱ አለመኖር
“በሁለት ነገሮች ነው። አንደኛው ታክቲካል ነው። ምክንያቱም አርባምንጭ ተከላካዯች ረጃጅሞች ናቸው። ስለዚህ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ወደ ሜዳ እገባለው ብዬ አላስብም። ሁለተኛ ደግሞ የተወሰነ መጠነኛ ጉዳቶች ነበሩ። የማገገሚያ ስራዎች እየሰራን ነው። ከፊታችን ብዙ ተድራቢ ጨዋታዎች አሉ። ዞሮ ዞሮ ዛሬ ሜዳ ውስጥ የነበሩ ልጆች ተቀይረው የገቡትም በሙሉ ጥሩ ነገር ሰርተዋል። በቀጣይም በሚኖሩ አምስት ጨዋታዎች ላይ የራሳችንን ስራ ሰርተን እንመጣለን።”
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ
ስለ ጨዋታው
“ጨዋታው መልካም ነው። የፈለግነውን ውጤት አላገኘንም። ከዚህ በላይ መንቀሳቀስ አለብን ፤ ችኮላዎች አሉ። ተረጋግተን የምንፈልገውን ለማድረግ ትዕግስት ይፈልጋል። ያን አይቻለው መታገስ አለብን የምንፈልገውን ለማግኘት ወይም ሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለማድረግ
ትዕግስት ያስፈልጋል።
የድሬደዋ ቆይታችሁ ምን እንዲሆን ታስባላቹሁ
“መልካም ነገር አስባለው። ያሉትን ችግሮች በየጊዜው የተለያዩ ነገሮች ያጋጥሙሀል ስህተትህን ተምረህ ነገ የተሻለ ነገር ይዘህ ለመቅረብ ትዕግስት ይፈልጋል። ያሉትን ነገሮች አርመን በቀጣይ እንቀርባለን።
የበዛ ጉጉት በተጫዋቾቹ ላይ ስለመታየቱ
“ያው ፍላጎቱ ኖሮም ዕውቀት ያስፈልጋል። የምታረጋቸውን ነገሮች በዕውቀት መስራት ይጠይቃል። እነዚህ ሁለቱ ነገሮች ሲዋሀዱ ነው ሁሉን ነገር የምናገኘው። ስለዚህ ፍላጎት አለ መንገዶችን ፈልገን ውጤት ለማምጣት ጠንክረን እንሰራለን።