[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የፊታችን ዓርብ ላበት ወሳኝ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን አጠናክሮ እየሰራ ይገኛል።
የሴቶች ከ20 ዓመት የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ለአራተኛው ዙር ማጣርያ የደረሰው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ታንዛንያ አቅንቶ በአንድ ጎል ልዩነት ተሸንፎ የመጣበትን ውጤት ለመቀልበስ ዝግጅቱን ከጀመረ ዛሬ ስድስተኛ ቀን ሆኖታል። ባሳለፍነው ቅዳሜ ከወንዶች ወጣት ቡድን ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ በዛሬው ዕለት ጨዋታውን በሚያከናውንበት አበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዱን ሰርቷል።
አብዛኛው የልምምዱ መርሐግብር የአካል ብቃት እና ታክቲካል ሥራዎችን ኳስ ጋር የሰራ ሲሆን ወደ መጨረሻው የልምምድ ጊዜ ለሁለት በመከፈል ሙሉ ሜዳ እንዲጫወቱ ተደርጓል። በእዚህ የእርስ በእርስ ጨዋታ ወቅት በተለይ በአንደኛው ቡድን የተካተቱት ተጫዋቾች በቀጣይ ጨዋታ በቡድኑ በመጀመርያው አሰላለፍ ውስጥ ይካተታሉ ተብሎ የሚገመቱ ተጫዋቾች ተመልክተናል።
ሶከር ኢትዮጵያ በዛሬው የልምምድ መርሐግብር እንደተመለከተችው የግብጠባቂዎች አሰልጣኝ የሆነው ፀጋዘአብ አስገዶም በቦታው ተገኝተው ግብጠባቂዎቹን ለጨዋታው የማዘጋጀት ተግባራቸውን ሲከውኑ ተመልክተናል። ከዚህ በተጨማሪ 20 ተጫዋቾችን በመያዝ ባሳለፍነው ሐሙስ በጀመረው ዝግጅት ውስጥ ያልነበሩት መስከረም ኢሳይያስ ፣ ማክዳ አሊ እና ቅድስት ቴካን በመጨመር አጠቃላይ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምድ ሲሰሩ ታዝበናል።
ለሁለት ሰዓት በቆየው እና የመለያ ምቶችን በመምታት በተቋጨው በዛሬ ልምምድ የቡድኑ አንበል እና ወሳኝ ተጫዋች ናርዶስ ጌትነት መጠናኛ ጉዳት አጋጥሟት ልምምዷን አቋርጣ ከመውጣቷ ውጭ ሁሉም የቡድኑ አባላት በመልካም ጤንነት ይገኛሉ። የፊታችን አርብ በአስር ሰዓት የመልሱን ጨዋታ የሚያደርገው ብሔራዊ ቡድናችን ውጤቱን በመቀልበስ ወደ አምስተኛው ዙርና የመጨረሻ ጨዋታ ለማለፍ በከፍተኛ ተነሳሽነት ልምምዳቸውን እየከወኑ እንደሚገኙ አይተናል።
ተጋጣሚያቸው የታንዛንያ ብሔራዊ ቡድን እስካሁን ያልገባ ሲሆን ምን አልባት ነገ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።