የቤትኪንግ ኢትዮጽያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ10ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች የሁለተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 አቤል ያለው ይህ ነው !

ቅዱስ ጊዮርጊስ ፋሲል ከነማን 4-0 በረመረመበት ጨዋታ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው አቤል ያለው ድንቅ የጨዋታ ዕለትን አሳልፏል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው የፋሲል ከተማን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ፋሲል ከነማዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ ይዘውት ለገቡት የጨዋታ ዕቅድ መሳካት የአቤል ያለው የጨዋታ ባህሪ በጣም የተመቸ ነበር። ፈጣን እና ቀጥተኛ ወደ ሳጥን የሚደረጉ ሩጫዎች መገለጫው የሆነው አቤል በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ የተቆጠሩትም ሁለት ግቦች ከላይ የጠቀስነው የተጫዋቹን የጨዋታ ባህሪ በግልፅ ያስመለከቱን አጋጣሚዎች ነበሩ።

ከአቤል ያለው ጋር በተወሰነ መልኩ ተቀራራቢ የሆነ የጨዋታ ባህሪ ያላቸው ፈጣን የመስመር አጥቂ/አማካዮችን/ የያዙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የእነዚህን ተጫዋቾች የጨዋታ ባህሪ ይበልጥ መጠቀም የሚያስችል የጨዋታ መንገድን በመዘርጋት ያላቸውን የማጥቃት አቅም ይበልጥ መጠቀም መቻል እና ያለመቻላቸው ጉዳይ በቀጣይ የቡድኑን የውድድር ዘመን ጉዞ የሚወስነው አንዱ ጉዳይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በመጨረሻዎቹ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ላይ የብሔራዊ ቡድኑ አባል የነበረው እና ከአፍሪካው ዋንጫው ስብስብ ውጪ መሆኑ ቁጭት እንደፈጠረበት ከጨዋታው በኋላ ሲናገር የተደመጠው አቤል በቀጣይም እንደ ቅዳሜው ዓይነት የሜዳ ላይ ብቃቱን በወጥነት መድገም ከቻለ የብሔራዊ ቡድን ተመራጭነቱን ማረጋገጥ የሚከብደው አይመስልም።

👉ቡድኑ ሲፈልገው የተገኘው ዳዊት እስጢፋኖስ

ጅማ አባ ጅፋር የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማ ላይ ማግኘት ችሏል። ታድያ ለዚህች ሦስት ነጥብ መገኘት የግቧ ባለቤት ዳዊት እስጢፋኖስ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

በ10 የጨዋታ ሳምንታት የዳዊት እስጢፋኖስን ግብ ሳይጨምር ከሁለት በላይ ግብ ማስቆጠር ያልቻለው ጅማ በአማካይ ሲታይ ምናልባት ሃያ ዓመትን በተሻገረው የሊጉ ታሪክ በዚህን ያህል ጨዋታ ብዛት ከተመለከትናቸው ደካማ የግብ ማስቆጠር ንፃሬዎች ተርታ የሚመደብ ሪከርድን ሳያስመዘግብ አይቀርም።

በመሆኑም ወጣቶችን ጥቂት ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ያጣመረው ቡድን ከሊጉ ግርጌ ለመላቀቅም ሆነ ይህን መጥፎ ጉዞ ለመቀልበስ ከቡድኑ ባለልምድ ተጫዋቾች አብዝቶ የሚጠብቅበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።

በተለይም በትልቅ ደረጃ በመጫወት እና የተለያዩ ስኬቶችን በቀደመው የእግርኳስ ህይወታቸው ማሳካት የቻሉት የመስዑድ መሀመድ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ እና የዳዊት ፍቃዱ አስፈላጊነት የሚጎላበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።

ምንም እንኳን ጅማ ማሸነፍ ባይችል እንኳን መስዑድ መሀመድ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ቡድኑን ለመርዳት የተቻለውን እያደረገ ቆይቷል። አሁን ደግሞ በመጀመሪያው ሳምንት በተፈጠረ አጋጣሚ በርከት ያሉ ጨዋታዎች ያመለጡት ዳዊት እስጢፋኖስ ወደ ቡድኑ ከተመለሰ ወዲህ የመስዑድ መሀመድን ኃላፊነት በመጋራት ረገድ የተሻለ ነገር ለመስራት እየታተረ ይገኛል።

ሜዳ ላይ ሁለቱ ተጫዋቾች ከሚታይባቸው ደመነፍሳዊ መግባባት ባለፈ ካላቸው የመሪነት አቅም ቡድኑ ከዚህ በላይ ይጠቅማል ተብሎ ይጠበቃል። ታድያ በሊጉ በቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ረገድ የተሻሉ ከሆኑ ተጫዋቾች ተርታ የሚመደበው ዳዊት እስጢፋኖስ ግብ ማስቆጠር ለተሳነው ጅማ አባ ጅፋር እጅግ ወሳኝ የነበረች የቅጣት ምት ግብ በማስቆጠር ለቡድኑ ተስፋን ፈንጥቋል።

በቀጣይም እነዚህ ባለልምድ ተጫዋቾች ለወጣቶች ምሳሌ እንደመሆናቸውም መጠን ቡድኑ ከተደቀነበት ፈተና ለማላቀቅ ከፍተኛ ኃላፊነት ትከሻቸው ላይ ወድቋል።

👉 የሲዳማ ቡና ማጥቃት ቁልፉ ሰው

ከሲዳማ ቡና ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ላይ በማጥቃቱ ረገድ በተለይ በመልሶ ማጥቃት እየተሻሻሉ ስለመምጣታቸው ስናስብ ቀዳሚው ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ተጫዋች የአጥቂ አማካዩ ፍሬው ሰለሞን ነው።

ብዙዎች የአጥቂ አማካዮች ያልታደሉትን አስደናቂ ታታሪነትን የተላበሰው ፍሬው በተለይ ከጥልቀት እየተነሳ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደራጅበት እንዲሁም ከጥልቀት መነሻቸውን ያደረጉ የተመጠኑ ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ በማድረስ የተሳካ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ከዚህ ባለፈም ሳይጠበቅ ዘግይቶ ወደ ሳጥኑ ውስጥ በሚያደርጋቸው ሩጫዎች የግብ አጋጣሚዎችንም ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው።

ከዓመታት ቆይታ በኋላ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭነት የተመለሰው ፍሬው በቀጣይም ሲዳማ ቡና የተሻለ የውድድር ዘመን የሚያሳልፍ ከሆነ የዚህ ተጫዋች አበርክቶ የላቀ እንደሚሆን ይጠበቃል።

👉 ሰዒድ ሀብታሙ ዳግም በሊጉ

በክረምቱ የዝውውር መስኮት የቀድሞ አሰልጣኙ ጳውሎስ ጌታቸውን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ የደረሰው ግብ ጠባቂ የሲሊቪያን ግቦሆ በአበረታች ቅመም መቀጣቱን ተከትሎ የጨዋታ ደቂቃዎችን እያገኘ ይገኛል።

ስለፈጣን የተጫዋቾች ዕድገት ስናነሳ ለአብነት መጥቀስ ከምንችላቸው ተጫዋቾች አንዱ ሰዒድ ሀብታሙ ነው። በ2011 የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊግ ተካፋይ በነበረው አርባምንጭ ከተማ የአሁኑ የወላይታ ድቻ ግብ ጠባቂ የሆነው የፅዮን መርዕድ ተጠባባቂ የነበረው ሰዒድ የፅዮን መጎዳትን ተከትሎ ባገኘው ዕድል ራሱን በማሳየቱ የተነሳ በ2012 ወደ ጅማ አባ ጅፋር ማምራቱ አይዘነጋም።

በጅማ አባ ጅፋር ሲጀምር የገጠመው ሂደት አስቸጋሪ ነበር። በወቅቱ መሀመድ ሙንታሪ እና ዘሪሁን ታደለ ከሰዒድ በተጨማሪ የያዙት ጅማዎች ለሰዒድ ከሦስተኛ ግብ ጠባቂነት የዘለለ ቦታ አልነበራቸውም። በአንድ አጋጣሚ ግን ሁለቱ ግብ ጠባቂዎች አለመኖራቸውን ተከትሎ ያገኘውን ዕድል ተጠቅሞ ሊጉ በኮቪድ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ድንቅ ጊዜያትን ማሳለፍ ችሏል።

ነገር ግን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ጅማ አባ ጅፋርን ለቆ ወደ ወላይታ ድቻ ያመራው ግብጠባቂው የድቻ ቆይታው የእግርኳስ ህይወቱን አንድ እርምጃ ወደ ኃላ የመለሰ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል። በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ከወላይታ ድቻ ጋር በስምምነት ተለያይቶ ያለ ክለብ ያሳለፈው ሰዒድ በክረምቱ ከቀድሞ አሰልጣኙ ጋር በወልቂጤ የሚያገናኘውን ዝውውር ፈፅሟል።

የወልቂጤ ከተማ ቀዳሚ ተመራጭ ግብጠባቂ የሆነው አይቮሪኮስታዊው ሲልቪያን ግቦሆ ‘አበረታች ቅመሞች ተጠቅሟል’ በሚል በፊፋ መቀጣቱን ተከትሎ ተከታታይ የጨዋታ ዕድሎችን እያገኘ የሚገኘው ሰዒድ ሀብታሙ የተንገራገጨውን የእግርኳስ ህይወቱን ዳግም ወደ መስመር ማስገቢያው አጋጣሚ ይህ ይመስላል።

የሲልቫይን የቅጣት ርዝመት አለመታወቁን ተከትሎ ምናልባት ሰዒድ በእነዚሁ ተከታታይ ጨዋታዎች የተሻለ የሜዳ ላይ ብቃቱን ማሳየት የሚችል ከሆነ ክለቡ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ወደ ገበያ እንዳይወጣ በማስገደድ ብቃቱን ፈልጎ የሚያገኝበትን እና በጅማ ከዚህ ቀደም አሳይቶን በነበረው ተስፋ እስከ ብሔራዊ ቡድን መመረጥ ያበቃውን ሂደት ለማስቀጠል የሚችልበትን ዕድል መፍጠር ይችላል ተብሎ ይገመታል።

👉የይስሃቅ ተገኝ ስህተት እንድምታዎች

ወጣቱ ግብ ጠባቂ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ጋሞ ጨንቻን ለቆ አርባምንጭ ከተማን መዳረሻው ካደረገ በኋላ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች የቡድኑ አንጋፋ ግብ ጠባቂ የሆነውን ሳምሶን አሰፋን ተከቶ እየተሰለፈ ይገኛል። ነገርግን በአንዳንድ ጨዋታ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ሲያድን የተመለከትነው ግብ ጠባቂ ሀገራዊ ህመማችን ከሆነው ከጊዜ አጠባበቅ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ስህተቶችን መስራቱ አልቀረም።

ቡድኑ በዚህ ሳምንት ወላይታ ድቻን ሲገጥም በመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ የቆሙ ኳሶችን ለመቆጣጠር ከግብ ክልሉ በሚወጣበት ቅፅበት ከቡድን አጋሮቹ የተግባቦት ችግር ይታይበት ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የወላይታ ድቻዎች ግብ የተገኘችበት የፍፁም ቅጣት ምት አጋጣሚም የወላይታ ድቻው አማካይ ሀብታሙ ንጉሴ ከመሀል ሜዳ አካባቢ ለማሻማት ወደ ፊት የላከውን ኳስ ግብ ጠባቂው በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሉ የፈጠረውን ስህተት ለማረም ባደረገው ጥረት ምንይሉ ወንድሙ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘ ነበር።

በእርግጥ ከግብ ጠባቂው ወጣትነት እና በሊጉ ልምድ ያላቸው ግብ ጠባቂዎች ላይ ከሚታዩ ስህተቶች አንፃር የድቻው ጨዋታ ብቃት በብዙ የሚያስወግዘው ላይሆን ይችላል። ከክለብ ባለፈ እንደሀገር ስንመለከተው ግን ሁኔታው ቀጣዮቹን ዓመታትም ከግብ ጠባቂዎች ብቃት አንፃር በስጋት እንድንመለከታቸው ያስገድደናል። አሁን ላይ የብሔራዊ ቡድን ተመራጭ የሆኑ የግብ ዘቦች በአፍሪካ ዋንጫ መድረክ እና በወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ እንደ ይስሀቅ ዓይነት ስህተቶችን በተደጋጋሚ ሰርተው ውጤት ስናጣ ያየንባቸው አጋጣሚዎች ገና ከትዝታችን አልደበዘዙም።

ነገ ትልቅ ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣት ግብ ጠባቂዎች በዚሁ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ምክንያት በሊጋችን ጨዋታዎች ላይ ያንኑ ስህተት ሲያስመለክቱን ግን የስልጠና መንገዳችንን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። የተሰራውንም ስህተት ከአንድ ግለሰብ ብቃት በላይ አልፈን እንድንመረምር የሚያደርገን ነው። በመሆኑም ከአርባምንጭ ውጪም ያሉ የሊጉ ክለቦች ወጣት ግብ ጠባቂዎቻቸውን ከዛሬ ነገ የተሻሉ ሆነው ከእነርሱ አልፈው ሀገራቸውን ለዓመታት በወጥነት የሚያገለግሉ እንዲሆኑ መሰል ስህተቶችን ከዕለታዊ ነጥብ ማጣት አንፃር ብቻ መዝነው ግብ ጠባቂውን ዕድል ወደመንፈግ ከመሄዳቸው በፊት ችግሩን ራቅ አድርገው በቁም ነገር በመውሰድ ከስር መሰረቱ መፍትሄ ለማምጣት የመስራት ኃላፊነት አለባቸው።

👉የብሩክ ሙሉጌታ ጎል

ሲዳማ ቡና ባህርዳር ከተማን ከመመራት ተነስቶ በረታበት ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች የአቻነቷን ግብ ያስቆጠሩበት መንገድ ግን አስገራሚ ነበር።

በ69ኛው ደቂቃ አማካዩ ዳዊት ተፈራን ተከትቶ ወደ ሜዳ የገባው የመስመር አማካዩ ብሩክ ሙሉጌታ የመጀመሪያ የጨዋታውን ተሳትፎ ለማድረግ ቡድኑ ያገኘውን የማዕዘን ምት ለመሻማት ወደ ሳጥን የደርሶ ፍሬው ሰለሞን ያሻማውን የማዕዘን ምት በመጀመሪያው የጨዋታ ንክኪ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

👉ጠፍቶ የከረመው አክሊሉ ዋለልኝ

በ2006 በአሰልጣኝ ወንድማገኝ ከበደ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ብሔራዊ ቡድን በአምበልነት እየመራ ራሱን ለእግርኳስ ቤተሰቡ ያስተዋወቀው አማካዩ አክሊሉ ዋለልኝ በፕሪሚየር ሊጉ ግን በሚፈለገው ደረጃ ዕድገቱን ማስቀጠል እየቻለ አይገኝም።

በክለብ ደረጃ በሀዋሳ ከተማ ጅማሮውን ያደረገው ተጫዋቹ በቀጣይ በኢትዮጵያ ቡና ከነበረው ቆይታ ባለፈ የተረጋጋ ጊዜን ማሳለፍ አልቻለም። በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወደ ሰበታ ከተማ ያቀናው አማካዩ በተለያዩ ምክንያቶች እስከ 10ኛ የጨዋታ ሳምንት ሳንመለከተው ቆይተናል።

ታድያ ቡድኑ በአዳማ ከተማ በተሸነፈበት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አክሊሉ እንደ ቡድን ከመከላከል ባለፈ የረባ እንቅስቃሴ ማድረግ ባልቻለው የሰበታ ከተማ ስብስብ ውስጥ በመጀመሪያ ተመራጭነት ጨዋታ ማድረግ ችሏል።

በ10ኛ ጨዋታ ወደ እንቅስቃሴ የተመለሰው አክሊሉ በቀጣይ ወደ ሊጉ ግርጌ እየተጠጋ በሚገኘው ሰበታ ከተማ ከዚህ ሂደት ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት የሚኖረው አበርክቶ ምን ድረስ ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ የምንመለከተው ይሆናል።

ያጋሩ