[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
”የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሳይሆን ደካማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ነው ደካማ”
”አቡበከር ይበልጣል ጌታነህ ይበልጣል? በእድሜም በኳስ ችሎታም?”
”…በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ካሉ ሊጎች ሁሉ ግዙፉ እና ጠንካራው ሊግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነው”
ትናንት ምሽት ከ10ኛ እስከ 15ኛ ሳምንት ድረስ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን እያስተናገደች የምትገኘው ድሬዳዋ ከተማ የ16ቱንም ክለብ ተወካዮች ፣ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችን በራስ ሆቴል የእንኳን ደህና መጣችሁ የእራት ግብዧ ዝግጅት አዘጋጅታ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። በመርሐ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ንግግር እንዲያደርጉ ዕድል ተሰጥቷቸው በወሬያቸው መሐል ያነሷቸው ነጥቦች የብዙሃኑን ትኩረት የሳበ ነበር። ሰብሳቢው ሊጉ ደካማ ነው የሚሉ ሀሳቦችን ተንተርሶ ያስተላለፉትን ንግግር እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
“በያዝነው የፈረንጆች ወር የውጪ መልማዮችን ለማምጣት ጥረት እያደረግን ነው። በዚህ ደግሞ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ከሀገር ወጥተው ከተጫወቱ ብሔራዊ ቡድናችን ይጠናከራል። የብሔራዊ ቡድን መጠናከር ብቻ ሳይሆን የተጫዋቾችም ገቢ በተሻለ ሁኔታ ያድጋል። ስለዚህ ክለቦች ጠንክራችሁ እንድትጫወቱ እንጠብቃለን። ፕሮፌሽናል ሆነው እንዲጫወቱም ማረግ አለባችሁ። ይሄ ሀላፊነት ደግሞ የሚወድቀው አሠልጣኞች ላይ ነው። በዚሁ አጋጣሚ እባካችሁ ብዬ የምለምነው ተጫዋቾቻችን ፕሮፌሽናል ለመሆም የሚያደርጉትን ጥረት እንድትደግፉ ነው። በዚህ ላይ እንዲሰራ። ሳይሰራ ምንም ነገር አይገኝም።
“የፕሪምየር ሊጉ እድገት በፋይናንስ ብቻ መለካት የለበትም። በተጫዋቾቻችን እና በዳኞቻችን ብቃት እንዲሁም በሌሎች ሌሎችም ነገሮች ይለካል። ስለዚህ በእኛ እና በሚያስተላልፉት ፕሮፌሽናሎች አመለካከት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ነው። እንደውም አንዳንዶቹ የሚሉት በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ካሉ ሊጎች ሁሉ ግዙፉ እና ጠንካራው ሊግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነው። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጎረቤታችን ካሉት ከታንዛኒያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ ይበልጣል።
“ባለፈው ጊዜ እጅግ በሚያሳዝን መልኩ እሳቸው ከተናገሩት እኔም ልድፈረው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሊጉ ደካማ ነው አሉ። እጅግ በጣም ያሳዝናል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሳይሆን ደካማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ነው ደካማ።
“አቡበከርን አንዳንድ ክለቦች የአፍሪካ ዋንጫው ላይ ተገኝተን እዛ እናስፈርመዋለን ብለው ነበር። ግን በማይታመን እና በማይታወቅ ምልኩ አቡበከር የመሐል አጥቂ ቦታ ላይ አልተገኘም። ክለቦቹም ጠይቀውናል። ለምንድን ነው ከቦታው የተነሳው ብለው። ግን ምንም መልስ የለም። አቡበከር ይበልጣል ጌታነህ ይበልጣል? በእድሜም በኳስ ችሎታም? ይሄ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምርጫ እና ቅንጅቱ እንዴት ነው? መቼስ አሠልጣኝ ባንሆንም ከ50 ዓመት በላይ የኢትዮጵያን እግርኳስ ተመልክተናል። የቀድሞ ክለቦችን ረግጦ የሚዘጋጅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሁን አይመጣም።”