[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በ10ኛ የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ የታዘብናቸው አሰልጣኞችን የተመለከቱ ጉዳዮች የዚህኛው ፅሁፋችን አካል ነው።
👉የሙሉጌታ ምህረት ቢጫ ካርድ
17 ዓመታትን በተሻገረው የተጫዋችነት ህይወቱ አንድ ቢጫ ካርድ ብቻ እንደተመለከተ የሚነገርለት ሙሉጌታ ምህረት በአሰልጣኝነቱ ደግም የመጀመሪያ ቢጫ ካርዱን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ተመልክቷል።
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን 2-1 እየመራ በነበረበት ወቅት በተለይም በሁለተኛ አጋማሽ የቡድኑ ተጫዋቾች ከማጥቃት ይልቅ ያገኙትን መሪነት ለማስጠበቅ ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸውን ተከትሎ በብስጭት አጠገቡ የነበረን የፕላስቲክ ውሃ ጠርሙስን በእግሩ በመለጋት ላሳየው ያልተገባ ድርጊት የቢጫ ካርድ ሰለባ ሆኗል።
የተረጋጋ ስብዕና ባለቤት የሆነው ሙሉጌታ በተጫዋችነት ዘመኑ አልቢትር ዓለማየሁ እሸቴ ብቸኛዋን የቢጫ ካርድ እንዳሳዩት ሲወሳ አርቢትር አሸብር ሰቦቃ ደግሞ የአሰልጣኝነት ህይወቱ ቀዳሚ ቢጫ ካርድ መዛዥ ሆነዋል። በእርግጥ በሀገራችን እግርኳስ ካለው ደካማ የመረጃ አሰባሰብ እና አደረጃጀት ሂደት አንፃር ይህንን ታሪክ በማስረጃ ማስደገፍ ከባድ ቢሆንም የአሰልጣኙ ቢጫ ካርድ መመልከት በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳበ ጉዳይ መሆኑ አይካድም።
👉የገብረመድህን ኃይሌ የደስታ አገላለፅ
ከሦስት ጨዋታዎች በፊት ስራቸውን ለማጣት ተቃርበው የነበሩት እና በሁለት ተከታታይ ዓመታት ከተለያዩ ክለቦች ጋር በመሆን የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ታሪክ የሰሩት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በሲዳማ ቡና ቤት ቀስ በቀስ የነፃነት አየርን መተንፈስ እየጀመሩ ይገኛል።
በተለይ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድናቸው ባህር ዳር ከተማን ከመመራት ተነስቶ በረታበት ጨዋታ ሁለተኛዋ የይገዙ ቦጋለ ግብ ስትቆጠር ያሳዩት የደስታ አገላለጽ ብዙ ነገሮችን የሚገልፅ ነበር።
ለወትሮው ከፊታቸው ገፅታ መለዋወጥ ባለፈ በሁለቱም ፅንፍ ያሉትን ስሜቶች በተጋነነ መልኩ ሲገልፁ የማንመለከታቸው አሰልጣኙ ግቧ በተቆጠረችበት ወቅት የተጫዋችነት ዘመናቸውን ያስታውሰ መጠነኛ ሩጫ የታከለበት የደስታ አገላለጽን ያስመለከቱን ሲሆን አስከትለው የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ላይ ዘለው የተንጠለጠሉበት መንገድ አስገራሚ ክስተት ነበር።
በውድድሩ ዘመን ጅማሮ አሰልጣኙ ካላቸው የሥራ ማህደር እና በሲዳማ ከያዙት ስብስብ አንፃር በብዙዎች በሰንጠረዡ አናት ለሚገኙ ስፍራዎች የተጫው ቡድኑ አጀማመሩ በሚፈለገው ልክ አልሆነለትም። አሁን ግን በተወሰነ መልኩ ነገሮች በሲዳማ ቤት መልክ እየያዙ ያለ ይመስላል። በመሆኑም አሰልጣኙ ብዙዎች በሚጠብቁት ደረጃ ወደ ፊት ያንደረድሩታል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
👉አብርሃምን የተካው አብርሃም
የካፍ ኤሌት ኢንስትራክተር የሆኑት እና ባህርዳር ከተማን በዋና አሰልጣኝነት እየመሩ የሚገኙት አብርሃም መብራቱ በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ የካፍ የቴክኒክ ኮሚቴ በመሆን ውድድሩን እንዲገመግሙ ወደ ስፍራው ማቅናታቸው ይታወሳል።
ታድያ የአፍሪካ ዋንጫ ግዳጃቸውን ያላጠናቀቁት አሰልጣኙ እስከ ውድድሩ መጠናቀቂያ ካሜሮን መቆየታቸውን ተከትሎ ቡድኑን በጊዜያዊነት እያሰለጠኑ የሚገኙት ምክትላቸው አብርሃም መላኩ ሲሆኑ ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ የጣና ሞገዶቹን እየመሩ ወደ ሜዳ መግባት ችለዋል።
ከጨዋታው በፊት ሲናገሩ እንደተደመጡት በጉዳት ምክንያት ስብስባቸው ስለመሳሳቱ ያነሱት አሰልጣኙ በዚህም መነሻነት አስቀድመው በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፉትን ተጫዋቾች ለማሳረፍ ቢያስቡም በጉዳት መነሻነት ተጫዋቾች ለመጠቀም መገደዳቸው እና በጨዋታውም በራሳቸው መንገድ ቡድኑን ይዘው እንደሚገቡ ገልፀው ነበር።
በመጀመሪያ አጋማሽ በተለይ በማጥቃቱ ረገድ የተሻለ የነበረው ቡድናቸው በሁለተኛው አጋማሽ ግን ወደ ኋላ በመሳቡ ጫናዎችን በመጋበዝ በስተመጨረሻም ሁለት ግቦችን አስተናግዶ ለመሸነፍ ተገዷል።
በሁለተኛው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ የተቀዛቀዘውን ቡድናቸውን ለማስተካከል አሰልጣኙ የወሰዷቸው ውሳኔዎች ጥያቄ የሚነሳባቸው ነበሩ። ቡድኑ ወደ ኋላ የማፈግፈግ አዝማሚያ ሲያሳይ ይህን ቢያንስ በፍላጎት ደረጃ ለመቅረፍ አዎንታዊ ቅያሬዎችን ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይልቁኑ ሁለተኛው አጋማሽ ብዙም ሳይገፋ ውጤቱን ለማስጠበቅ የሚረዱ አሉታዊ ቅያሬዎችን ሲያደርጉ መመልከታችን ጫናው እንዲያይልባቸው እና ግቦች እንዲቆጠሩ ምክንያት ነበር ብሎ ማንሳት ይቻላል።
እርግጥ አሰልጣኙ በዚህ ደረጃ በማሰልጠን በቂ ልምድ እንደሌላቸው ቢታመንም በቀጣይ ዋና አሰልጣኝ እስኪመጡ ቡድኑን በሚመሩባቸው አንድ አልያም ሁለት ጨዋታዎች ይህን የጨዋታ ወቅት አስተዳደራቸውን ማሻሻል ይጠቅባቸዋል።
👉የአሰልጣኝ መሳይ የተቀዛቀዘ የጨዋታ ዕለት አመራር
“መከባበር” የሚለው አሳቤ በሀገራችን እግርኳስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ቦታ የሌለው እስኪመስል ይህ ስፖርታዊ መርህ በተለይ በእግርኳሳችን ቦታ ሲሰጠው አይስተዋልም። ሀሳቡ በጣም ከመጥፋቱ የተነሳ ክብር የሚሰጡ ሲገኙ በትልቅ ደረጃ ማስተጋባት እየተለመደ መጥቷል።
የቀድሞ ክለባቸው ላይ አስቆጥረው ደስታቸውን የሚገልፁ ፣ በቃለ መጠይቆች ላይ የቀድሞ ቀጣሪዎችን በነገር መሸንቆጥ እና ሌሎችም በመሰረታዊነት ስህተት ያልሆኑ ነገርግን አመክንዮአዊ ያልሆነ ድርጊቶች በተደጋጋሚ እየተመለከተን ቀጥለናል። በተቃራኒው ግን ለተደረገላቸው ነገር ክብር እና እውቅና የሚሰጡትን ማግኘቱ ፈታኝ ነው።
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለዘጠኝ ዓመታት የሰሩበትን ወላይታ ድቻን በተቃራኒ አርባምንጭ ከተማን ሲገጥሙ በቅድመ ጨዋታ ቃለ መጠይቃቸው ሲናገሩ እንደተደመጡት የተለየ ክብር እንዳላቸው እና እንደ ተጫዋቾች ሁሉ ደስታቸውን ባለመግለፅ ይህን እንደሚያሳዩ ገልፀው ነበር።
ነገር ግን በጨዋታው የተመለከትነው ጉዳይ ትንሽ የሚያነጋግር ነው። ለወትሮው በሜዳው ጠርዝ ቡድናቸው ጨዋታ ሲያደርግ እየተቁነጠነጡ ቡድናቸውን በመምራት የሚታወቁት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በዚህኛው ጨዋታ ለውሀ ዕረፍት በሁለት አጋጣሚዎች ጨዋታው ከተቋረጠባቸው አጋጣሚዎች ውጪ ከወንበራቸው ተነስተው ተጫዋቾች ሲመሩ እና ትዕዛዞችን ሲሰጡ አልተመለከትንም። ያልተለመደው የተቀዛቀዘ ሜዳ ላይ አመራራቸው ከሌሎች ከብዙ ምክንያቶች ጋር ተያይዞ የትከሰተ ሊሆን እንደሚችል ቢታወቅም ከቀድሞው ክለባቸው ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ በመስተዋሉ ግጥምጥሞሹ ትኩረት ሳቢ ሆኖ ተመልክተነዋል።