ሻሸመኔ ከተማ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

የአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ ሻሸመኔ ከተማ ተጨማሪ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን በዛሬው ዕለት የግሉ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላ የተሳትፎ ዕድልን ያገኘው ሻሸመኔ ከተማ በአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ አማካኝነት ከቀናቶች በፊት ቻላቸው መንበሩ ፣ እዮብ ገብረማርያም እና ሙሉቀን ታሪኩን በይፋ ያስፈረመ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የአራት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ዝውውር ስለማጠናቀቁ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ሔኖክ ድልቢ አዲሱ የሻሸመኔ ተጫዋች ሆኗል። ከሀዋሳ ከተማ ወጣት ቡድን የተገኘው እና በዋናውም ቡድን ተከታታይ ዓመትን በመጫወት አማካዩ ግልጋሎት መስጠት የቻለ ሲሆን የተጠናቀቀውን ዓመት በኢትዮጵያ ቡና ቆይታን ያደረገ ሲሆን ከክለቡ ጋር ቀሪ ውል እያለው በስምምነት ከተለያየ በኋላ መዳረሻው ሻሸመኔ ሆኗል።

ሌላኛው ፈራሚ የግብ ዘቡ መስፍን ሙዜ ነው። ከሀዋሳ ወጣት ቡድን መነሻውን ያደገው እና በኢኮስኮ ፣ ወልድያ ፣ ባቱ እና የ2015 የውድድር ዓመትን ከቤንች ማጂ ቡና ጋር ጥሩ የውድድር ዓመት አሳልፎ ወደ አዲስ አዳጊው ክለብ አምርቷል።

ሌላኛው ፈራሚ ወጣቱ የመስመር አጥቂ ታምራት ስላስ ሆኗል። ከወላይታ ድቻ ወጣት ቡድን መነሻውን ያደገው እና በሀምበሪቾ ፣ ነቀምት እና ንብ የተጫወተው ተጫዋቹ አዲስ አዳጊውን ክለብ የተቀላቀለበትን ዝውውር ቋጭቷል።

ሰባተኛው አዲስ ተጫዋች የግራ መስመር ተከላካዩ አሸብር ውሮ ነው። በአርባምንጭ ከተማ ፣ አክሱም ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ (ይርጋጨፌ ቡና) የተጫወተው እንዲሁም የተጠናቀቀውን ዓመት በባቱ ከተማ አሳልፎ ሻሸመኔን ተቀላቅሏል።