[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በ10ኛው ሳምንት ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ የተንቀሳቀሱ ተጫዋቾችን እንደሚከተለው መርጠናል።
አሰላለፍ : 4-2-3-1
ግብ ጠባቂ
ፍሬው ጌታሁን – ድሬዳዋ ከተማ
በአጠቃላይ የተቆጠሩ ግቦች በርከት ባሉበት ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አምስት ግብ ጠባቂዎች መረባቸውን ያላስደፈሩ ሲሆን ከመሀላቸው ፍሬውን በስብስባችን አካተናል። በተለይም መከላከያን ወደ መሪነት ሊያሸጋግሩ የቀረቡ እጅግ ለግብ የቀረቡ የኢብራሂም ሁሴን እና ልደቱ ጌታቸውን ኳሶች ያዳነበት ቅልጥፍና በጠባብ ውጤት ባለቀው ጨዋታ ላይ ልዩነት ፈጥሯል።
ተከላካዮች
ብርሀኑ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
ሀዲያ ሆሳዕና ባለቀ ሰዓት አቻ በተለያየበት የዚህ ሳምንት ጨዋታ በግል ጥሩ ከተነቀሳቀሱ ተጫዋቾች መሀል በመሰመር ተመላላሽነት ተሰልፎ የነበረው ብርሀኑ አንዱ ነው። ከፍ ባለ የማጥቃት ተሳትፎ ቡድኑን ያገለገለው ተጫዋቹ ከቦታው ሌሎች አማራጮች አንፃር የተሻለ ግልጋሎት ሲሰጥ ሆሳዕናን መሪ ያደረገችውን ጎል የግል ብቃቱን አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ ተከላካዮችን አታሎ ማመቻቸት ችሎ ነበር።
መሳይ ጳውሎስ – ድሬዳዋ ከተማ
ድሬዎች ወደ ከተማቸው በተመለሰው ውድድር ቀዳሚ ሦስት ነጥቦችን ባሰኩበት ጨዋታ የመከላከል ቅርፃቸው ተሻሽሎ ታይቷል። በዚህ ውስጥ ደግሞ የመሀል ተከላካዩ መሳይ አብሮት ከተሰለፈው ወጣቱ አቤል አሰበ ጋር በመሆን ቀጥተኛ አጨዋወት የሚከተለው መከላከያን አደገኛ ኳሶች ፍሬ እንዳያፈሩ በማድረግ ጥሩ ቀን ሲያሳልፍ አንድ ለግብ የቀረበ ኳስም ከግብ አፋፍ አውጥቷል።
ላውረን ላርቴ – ሀዋሳ ከተማ
በሉጉ ውስጥ ከቆዩ የውጪ ዜጎች ውስጥ በአንፃራዊነት ወጥ ብቃት በማሳየት የሚነሳው ላውረንስ ሀዋሳ ቡናን ሲረታ በጥሩ ትኩረት ጨዋታውን ከውኗል። ባልተዛነፈ የጊዜ አጠባበቅ እና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የበላይ በመሆን የኢትዮጵያ ቡና ቅብብሎች ወደ ሳጥን ደርሰው ወደ ተደጋጋሚ የግብ አጋጣሚነት እንዳይቀየሩ የሚጠበቅበትን አድርጓል።
ደስታ ዮሐንስ – አዳማ ከተማ
በዚህ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች በመጫወቻ ቦታ ብዙ ይቱጫዋቾች አማራጭ ያልነበረው በግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ነበር። ሆኖም ከዋሊያዎቹ ጋር ከነበረው የካሜሩን ቆይታ መልስ አዳማ ከመመራት ተነስቶ ድል ባደረገበት ጨዋታ እጅግ ወሳኝ የነበራችው ሀለተኛ ግብ እንድትቆጠር አመቻችቶ ማቀበል የቻለው ደስታን ተመራጭ አድርገነዋል።
አማካዮች
አብዱልባስጥ ከማል – ሀዋሳ ከተማ
ከተከላካይ መስመሩ ፊት ከበቃሉ ገነነ ጋር ተጣምሮ የተጫወተው አብዱልባስጥ እጅግ ንቁ ሆኖ የታየበትን ጨዋታ አሳልፏል። የቡናን የኳስ ቅብብሎች ስኬት እንዲወርድ በማድረግ ቡድኑ እንዳይጋለጥ ከማገዝ ባለፈ በፍጥነት ወደፊት በመሄድ በነበረው የማጥቃት ተሳትፎ ሁለት ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችል አንደኛው የሀዋሳን ድል ወደማረጋገጥ የወሰደ ሁለተኛ ግብነት ተለውጧል።
ጋቶች ፓኖም – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ግዙፉ የተከላካይ አማካይ ቡድኑ በግብ በተንበሸበሸነት የጨዋታ ቀን የፋሲል ከነማ የኳስ ቅብብሎች ፍሬ እንዳያፈሩ ምክንያት የሆነ ብቃትን አሳይቷል። ጋቶች ኳሶችን በማቋረጥ በቶሎ ማጥቃትን ያስጀምርበት በነበረበት አኳኋን የጨዋታ ዕቅዱን ያሳልጥ የነበረ ሲሆን በአንደኛው ግብ መገኘት ላይም ነጥቆ በማቀበል ቀጥተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል።
ዳዊት እስጢፋኖስ – ጅማ አባ ጅፋር
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የተቀመጠው ጅማ የረጅም ጊዜ ልምድ ባለቤት የሆነው አማካዩን አስተዋፅዖ በቅጣት ምክንያት ሳያገኝ ቢቆይም ወደ ሜዳ በተመለሰ ሁለተኛ ጨዋታው ላይ ዳዊት ልዩነት መፍጠር ችሏል። የአማካይ ክፍሉን የኳስ ፍሰት ከማደራጀት ባለፈ የስቆጠረው የቅጣት ምት ጎል ከቡድኑ ውጤት ማጣት አንፃር ሲመዘን ዋጋው ከፍ ያለ በመሆኑ በቡድናችን ውስጥ እንዲካተት ሆኗል።
ፍሬው ሰለሞን – ሲዳማ ቡና
የሲዳማ የአማካይ ክፍል ቁልፍ ሰው የሆነው ፍሬው ሰለሞን በአስረኛው ሳምንት ቡድኑ ባህር ዳርን ባሸነፈበት ጨዋታም በታታሪነት የተሞላ ብቃትን አስመልክቶናል። ከጥልቅ የአማካይ ክፍል ኳሶችን ወደ ፊት ከማድረስ ወደ ሳጥን በመድረስ የግብ ሙከራ እስከማድረግ በዘለቀበት ጨዋታ የማሸነፊያዋ ጎል እንድትቆጠር ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ቡድኑን ለድል አብቅቷል።
አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ለአቤል ያለው በልኩ የተሰፋ በነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ የጨዋታ ዕቅድ ውስጥ ከቀኝ የሜዳው ወገን ወደ ውስጥ አጥብቦ መግባት የሚሆንለት አቤል ያለው ደምቆ ታይቷል። በጥሩ የአጨራረስ ብቃት ላይ በመገኘትም ዕለቱን ያሳለፈው ተጫዋቹ የቡድኑን የተሳኩ የማልሶ ማጥቃት ሂደቶች በማሳመር ሁለት ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል።
አጥቂ
ኢስማኤል ኦሮ- አጎሮ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ፈረሰኞቹ በፋሲሉ ጨዋታ በመልሶ ማጥቃት ብርቱ በትር በተጋጣሚያቸው ላይ እንዲያሳርፉ የፊት መስመራቸውን አስፈሪነት የሚያጎላ ሁነኛ ሰው ያስፈልጋቸው ነበር። በዚህም ቶጓዊው አጥቂ የቡድኑ የማጥቃት ቅፅበቶች ላይ የራሱን ሚና ሲወጣ የቆየ ሲሆን ሁለት ግቦችንም ከመረብ በማገናኘት የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት ደረጃ በብቸኝነት መምራት ጀምሯል።
አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
በ10ኛው ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች ውስጥ ከባድ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቅ የነበረውን ጨዋታ በሰፊ ጎል ማሸነፍ የቻሉት አሰልጣኝ ዘሪሁን ያለብዙ ሽሚያ የሳምንቱ ምርጣችን ሆነዋል። ዋና አሰልጣኞች በሚለቁባቸው ወቅቶች ቡድኑን ሲመሩ የሚስተዋሉት አሰልጣኙ በግልፅ በሚታይ እና ወጤታማ ሆኖ በዋለ የጨዋታ ዕቅድ ወሳኙን ጨዋታ አሸንፈው ሊጉን መምራት ጀምረዋል።
ተጠባባቂዎች
ተክለማሪያም ሻንቆ – ሲዳማ ቡና
ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ተስፋዬ አለባቸው – ሀዲያ ሆሳዕና
የአብስራ ተስፋዬ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
አማኑኤል ገብረሚካኤል – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሀብታሙ ገዛሀኝ – ሲዳማ ቡና
አብዱርሀማን ሙባረክ – ድሬድዋ ከተማ