​የተጫዋች ታምሩ ባልቻ ድንገተኛ ዜና እረፍት 

በከፍተኛ ሊግ የተለያዩ ክለቦች ሲጫወት የምናውቀው ታምሩ ባልቻ በድንገተኛ ህመም በዛሬው ዕለት ህይወቱ አልፏል።

በሰበታ አቅጣጫ ተጂ ከተማ የተወለደው ታምሩ ባልቻ በሠፈር የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱን በማሳደግ ወደ ተለያዩ ክለቦች የመጫወት ዕድሎችን በማግኘት  ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የሚወደውን እግርኳስ ሲጫወት ቆይቷል። በዘንድሮ ዓመት የከፍተኛ ሊግ በምድብ ለ ሰበታ ከተማ ላይ አንደኛው ዙር እስኪጠናቀቅ ድረስ ለሰንዳፋ በኬ በአጥቂ መስመር ላይ ተቀይሮ በመግባት ጎሎችን በማስቆጠር ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋች መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ በየጨዋታዎቹ በመገኘት መታዘብ ችላ ነበር።

ታምሩ እግርኳስን አየተጫወተ የጤና እክል ያጋጥመው መሆኑን ለሰንዳፋው በኬ አሰልጣኝ ዘንድሮ ይናገር እንደነበረ አሰልጣኙም ይህን በመረዳት የተወሰኑ ደቂቃዎች ቀይረው በማስገባት ይጠቀሙበት እንደነበረ እና የውድድሩ አጋማሽ የመጨረሻ ጨዋታ ወቅት ህመሙ አገርሽቶበት የቡድን አጋሮቹ ወደ ሆስፒታል ይዘውት እንደሄዱ ታውቋል። የህክምና ባለሙያዎቹም የልብ ህመም እንደሆነ እና በቂ እረፍት እንዲያደርግ ገልፀውለት እንደነበረ የቅርብ ወዳጆቹ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

ታምሩ የተወሰነ እረፍት ካደረገ በኋላ ለሁለተኛው ዙር ውድድር ዘመን ሰንዳፋ በኬን ለማገልገል እየተዘጋጀ በዛሬው ዕለት ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር እግርኳስን ተጫውቶ ወደ ቤቱ በማቅናት ጋደም ባለበት በአሳዛኝ ሁኔታ ላይመለስ ህይወቱ ማለፉን ሰምተናል። ከዚህ ቀደም ለሀላባ ከተማ፣ ለጌዲኦ ዲላ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ ለኢኮስኮ፣ ለየካ ክ/ከተማ ዘንድሮ ለሰንዳፋ በኬ ግልጋሎት የሰጠው ታምሩ ባልቻ ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በትውልድ ከተማው ተጂ ከተማ ነገ በዕለተ ሐሙስ ጥር 26 ቀን በመድኃኒዓለም ቤ/ክ ግብዐተ መሬቱ የሚፈፀም ይሆናል።

ሶከር ኢትዮጵያ በታምሩ ባልቻ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቹ ለወዳጅ ዘመዶቹ ለስፖርት ቤተሰቡ በሙሉ መፅናናትን ትመኛለች።