[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ በታዳጊዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራው ሀሌታ የታዳጊዎች የእግርኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት ጋር የአጋርነት ስምምነት ፈፅሟል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚሳተፉ 16 ክለቦች ከ12ቱ ጋር ስራዎችን እየሰራ የሚገኘው ግዙፉ ሀገር በቀል የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ከከፍተኛ ሊግ፣ አንደኛ ሊግ እና ብሔራዊ ሊግ እንዲሁም ከሴቶች ክለቦች ጋር መጠነ ሰፊ የትጥቅ አቅርቦት ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል። በአቶ ሳሙኤል መኮንን የተመሰረተው ተቋም ለታዳጊ ቡድኖች ትኩረት በመስጠት በርካታ ታዳጊዎችን በማፍራት ላይ ከሚገኘውን ሀሌታ የታዳጊዎች የእግርኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት ጋር ደግሞ በጋራ ለመስራት ስምምነት ፈፅመዋል።
2011 ላይ የተመሰረተው ሀሌታ የታዳጊዎች የእግርኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት ከ17፣ 14 እና 10 ዓመት በታች ቡድኖችን በማዋቀር ተተኪ ተጫዋቾችን ለማውጣት እየጣረ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከ17 ዓመት በታች ቡድኑም በኢትዮጵያ እግርኳስ ገናና ስም ካላቸው ክለቦች ጋር ከ17 ዓመት በታች ውድድርን እያደረገ ይገኛል። ታዲያ አሁን በብዙሃኑ ክለቦች ቀዳሚ ተመራጭ ከሆነው ጎፈሬ ጋር አብሮ ለመስራትም የሦስት ዓመት የአጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል። የስምምነቱን ይዘት ለድረ-ገፃችን ያስረዱት አቶ ሳሙኤል ለሦስቱም ቡድኖች (ከ17፣ 14 እና 10 ዓመት በታች) የመጫወቻ ትጥቅ የሚሰጥ ሲሆን በውድድር ላይ ለሚሳተፈው ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ ደግሞ የሜዳ እና ከሜዳ ውጪ መለያ እንዲሁም የመለማመጃ መለያ እንደሚሰጥ አመላክተውናል። ከዚህ በተጨማሪም በስምምነቱ ዝርዝር ውስጥም የደጋፊዎችን ማሊያዎች እንደሚቀርብ እንደተገለፀ ተነግሮናል።
የሀሌታ የታዳጊዎች የእግርኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት መስራች እና አሠልጣኝ አብይ ካሣሁን በበኩላቸው ስምምነቱን ተከትሎ ስሜታቸውን በተከታዩ መልኩ አጋርተውናል። “ሀሌታ ማለት የመጀመሪያ ማለት ነው ። እንደ ስማችን በታዳጊ ቡድኖች ደረጃ ከትጥቅ አምራች ድርጅት ጋር በመስራት የመጀመሪያ በመሆናችን ደስታ ይሰማናል። በሀገራችን ኢትዮጲያ ግዙፍ ትጥቅ አምራች ከሆነው ጎፈሬ ጋር በመስራታችን ደግሞ ኩራት ተሰምቶናል። በእግር ኳስ ዘላቂ ውጤት ለማምጣት ታዳጊዎች ላይ መስራት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው። ይህንን የአካዳሚያችንን ህልም ተረድቶ ጎፈሬ ከኛ ለመስራት በመወሰኑ ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ።”