ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር ተከታታይ ድሉን አሳክቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

አዝናኝ እንቅስቃሴ በታየበት የ11ኛ ሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ሀዲያ ሆሳዕናን 4-2 መርታት ችሏል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከወልቂጤው ሽንፈት ባደረጋቸው ሁለት ለውጦች እሸቱ ግርማን በኤልያስ አታሮ እንዲሁም ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን በአበባየሁ ዮሐንስ ተክቷል። አዲስ አበባን በመርታት የመጀመሪያ ድሉን ያሳካው ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስን በዮሐንስ በዛብህ ፣ ሽመልስ ተገኝን ከብዙ ውዝግቦች በኋላ የጅማ ተጫዋች በሆነው እያሱ ለገሰ ፣ ጉዳት ገጥሞት የነበረው ሙሴ ካበላን በበላይ አባይነህ እንዲሁም ዳዊት ፍቃዱን በዱላ ሙላቱ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።

ነቃ ብሎ በጀመረው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጫን ብለው የታዩ ሲሆን ወደ ሁለቱ ሳጥኖች የሚጣሉ ረጅም ኳሶች ፍልሚያው ቀላል እንደማይሆን ፍንጭ የሚሰጡ ነበሩ። ጨዋታው አጀማመሩን በሚመጥን መልኩ በቶሎ ግቦችን ማስተናገድም ችሏል። 5ኛው ደቂቃ ላይ የዱላ ሙላቱ የማዕዘን ምት በተከላካዮች ተጨርፎ ሲወጣ እዮብ ዓለማየሁ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ መትቶት እና በተስፋዬ መላኩ ተጨርፎ ጅማ አባ ጅፋር ቀዳሚ የሆነበት ግብ ተቆጥሯል። 

ወደ ባዬ ገዛኸኝ በሚደርሱ ኳሶች አጋጣሚዎች ለመፍጠር የተንቀሳቀሱት ነብሮቹ መረጋጋት ተስኗቸው ሲታዩ ጅማዎች በእዮብ እና ተስፋዬ ተከታታይ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለይም እዮብ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ይዞ በግራ በኩል ሳጥን ውስጥ ደርሶ ያደረገው ሙከራ በሶሆሆ ሜንሳህ ለጥቂት የዳነ ነበር።

ሆሳዕናዎች ምላሽ ለመስጠት ባደረጉት ጥረትወደ ጅማ ሳጥን በቶሎ መድረስ ችለዋል። በዚህም 14ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ጅማዎች ከሳጥናቸው አቅራቢያ በአበባየሁ ዮሐንስ የተነጠቁትን ኳስ ከሀብታሙ ታደሰ በመቀባበል አምልጦ ገብቶ ወደ ግብ ሲሞክር ኳስ ሁለቱን ቋሚዎች ገጭታ ስትመለስ የጅማዎቹን ወንድምአገኝ ማርቆስ እና ዮሐንስ በዛብህን ጨርፋ መረብ ላይ አርፋለች። ሆኖም ጅማዎች ዳግም መሪ ለመሆን የፈጀባቸው አራት ደቀቃ ብቻ ነበር። ለመሀመድ ኑር ናስር የተላከውን ኳስ አጥቂው ለመጠቀም ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቢቀርም በላይ አባይነህ መልሶ ሲሞክረው ሶሆሆ ሜንሳህ መቆጣጠር ተስኖት በራሱ ላይ አስቆጥሯል።

ግለቱ በግቦች የታጀበው ጨዋታ በማጥቃት ምልልስ ቀጥሎ ከውሀ ዕረፍት መልስም ጥሩ እንቅስቃሴን አሳይቶናል። ሀዲያ ሆሳዕናዎች በቀኝ ተመላላሻቸው ብርሀኑ በቀለ በኩል አድልተው ጫና ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።
ለዚህ አካሄድ በጥሩ የኳስ ውጪ እንቅስቃሴ ምላሽ ይሰጡ የነበሩት ጅማዎች ግን ይበልጥ አደገኛ ሆነው ይታዩ ነበር። የጨዋታው ሌላ ትኩረት ሳቢ ሂደት 33ኛው ደቂቃ ላይ ሲታይ ቶጓዊው የሆሳዕና ግብ ጠባቂ ከሳጥን ውጪ ወጥቶ ኳስ ለማራቅ ያደረገው ጥረት ለጅማማዎች ሌላ ግብ ለመፍጠር ተቃርቦ ነበር። ጅማ አባ ጅፋሮች የተጋጣሚያቸው ወደ ቀኝ ያደላ የኳስ ቁጥጥርን ባገኟቸው አጋጣሚዎች እያቋረጡ ወደ ፊት በመሄድ አደጋ ለመፍጠር ጥረዋል። በተለይም 36ኛው ደቂቃ ላይ በላይ አባይነህ ከቀኝ መስመር ያደረሰውን የተመጠነ ኳስ ዱላ መላቱ ወደ ግብ ቢልከውም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች ሌላ የግብ ዕድል ባይፈጠርባቸውም ፍልሚያው ለተመልካች ማራኪ ሆኖ የቀጠለ ነበር።

ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ፍጥነት እንደቀድመው ባይቀጥልም ፍክክሩ የቀጠለ ግጭቶችም የተበራከቱበት ነበር። በእንቅስቃሴው ሆሳዕናዎች በአመዛኙ ኳስ ይዘው ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ ጅማዎች ጥንቃቄ ጨምረው ቀርበዋል። በዚህም የነብሮቹ ሙከራዎች ከሳጥን ውጪ ይደረጉ የነበረ ሲሆን 57ኛው ደቂቃ ላይ በላይ አባይነህ ከማዕዘን የመጣን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚ አደገኛ የሚባል ዓይነት ነበር። ውጤት ለማስጠበቅ ሙሉ በሙሉ ማፈግፈግን ምርጫቸው ያላደረጉት ጅማዎች የመልሶ ማጥቃት ሂደቶች እየታዩ ቆይተው 65ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛው ግብ ተቆጥሯል።

መሀመድኑር በግራ በኩል ከጅማ አጋማሽ ጀምሮ ሳጥን ድረስ ያመጣው ኳስ በአማካዮቹ መስዑድ እና ዳዊት ጥምረት ሲመቻች ሳጥን ውስጥ እዮብ ዓለማየሁ ተረጋግቶ በመጨረስ ግብ አድርጎታል። ጅማዎች ከሦስት ደቂቃ በኋላም በበላይ አባይነህ ወደ ቀኝ ያደላ ቅጣት ምት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው በሶሆሆ ሜንሳህ ድኖባቸዋል። ሆኖም 74ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ከሀዲያ ሆሳዕናዎች ያስጣለውን ኳስ ከተከላካዮች ጀርባ ሲያሻግርለት መሀመድ ኑር በሶሆሆ ሜንሳህ አናት ላይ በማሻገር አራተኛውን ግብ ከመረብ አገናኝቷል። 

ጨዋታው ወደ ፍፃሜው ሲቃረብ በርካት ያሉ ቅያሪዎችን ያደረጉት ጅማዎች የመልሶ ማጥቃት ሂደቶች እየቀነሱ ቢመጡም ኳስ በመያዙ የተሻሉ የሆኑት ሆሳዕናዎች ጥቃት የመጨረሻ ዕድል ለማግኘት ብዙ ደቂቃ ወስዶባቸዋል። 90ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሆሳዕናዎች በሳጥኑ አቅራቢያ ያቋረጡን ኳስ ሳምሶን ጥላሁን ሰንጥቆለት ተቀይሮ የገባው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን አምልጦ በመግባት ግብ አድርጎታል። ድራማዊው ጨዋታ ቀጥሎ ሆሳዕናዎች ሚካኤል ጆርጅ ላይ በተሰራ ጥፋት በጭማሪ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ሄኖክ አርፌጮ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አዝናኙ ጨዋታም በጅማ የ4-2 የበላይነት ተቋጭቷል።

ሁለተኛ ተከታታይ ድል ያስመዘገበው ጅማ አባ ጅፋር ነጥቡን 7 በማድረስ ከበላዩ ካለው ሰበታ ከተማ ጋር ተስተካክሏል።

ያጋሩ