ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ አራተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ11ኛ የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የምሽት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባህርዳር ከተማን 2-0 በመርታት ነጥቡን ወደ 23 ከፍ በማድረግ መሪነቱን አጠናክሯል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ፋሲል ከነማን ከቀናት በፊት ካሸነፈው ስብስብ ምንም ቅያሬን ሳያደርጉ ጨዋታውን ሲጀምሩ ባህር ዳር ከተማዎች ግን ጉዳት ባስተናገደው መናፍ ዐወል ምትክ አማካዩን አለልኝ አዘነ ብቻ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታው ጅማሮውን ያደረገው በጎል ነበር ፤ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ በረጅም ወደ ባህርዳር አጋማሽ ካደረሳት ኳስ መነሻውን ባደረገው ሂደት አማኑኤል ገ/ሚካኤል ኳስ ወደ ግብ ሲልክ እና በአቡበከር ኑሪ ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው አቤል ያለው በቀላሉ በማስቆጠር ቡድኑ አስደናቂ አጀማመር እንዲያደርግ አስችሏል።

በዚህ መልኩ ጅማሬውን ባደረገው ጨዋታ ባህርዳር ከተማዎች አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢኖራቸውም በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የመድረስ ፍላጎት የነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው ውጤት በሚወስኑ ቅፅበቶች ላይ የተሻሉ ነበሩ።

በዚህም በ18ኛው ደቂቃ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ፍሪሞፖንግ ሜንሱ በረጅሙ ወደፊት ያሻገውን ኳስ ሰለሞን ወዴሳ ወደ ኃላ ለግብ ጠባቂያቸው አቡበከር ኑሪ ሲመልስ አቡበከር በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሉ የተገኘውን ኳስ ተጠቅሞ ከነዓን ማርክነህ በተረጋጋ አጨራረስ ሁለተኛውን ግብ ለቡድኑ ማስቆጠር ችሏል።


በመልሶ ማጥቃት አስፈሪ የነበሩት ፈረሰኞቹ በአጋማሹ ተጨማሪ ግብ ሊያስቆጥሩ የሚችሉባቸውን ተጨማሪ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። በሁለት አጋጣሚዎች ፍሪምፖንግ ሜንሱ ከቆሙ ኳሶች እንዲሁም አቤል ያለው ከተከላካይ ጀርባ ከተጣሉ ኳሶች ሳይጠቀሙባቸው የቀሯቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።
በመጀመሪያዎቹ 35 ደቂቃዎች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን ለመድረስ የተቸገሩት ባህርዳር ከተማዎች በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች የተሻለ የማጥቃት ጥረትን ሲያደርጉ ተመልክተናል ፤ በእነዚህም ደቂቃዎች በፍፁም ዓለሙ እና አብዱልከሪም ኒኪማ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር።

ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በጣም የተቀዛቀዝ መልክ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው አንፃር በተለይ በግብ ሙከራዎች ረገድ የወረደ ነበር።

እንደመጀመሪያው ሁሉ ባህርዳር ከተማዎች የነበራቸውን አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ማስቀጠል ቢችሉም ከኳስ ውጭ በቁጥር በርከት ብለው ለመከላከል ጥረት ሲያደርግ የነበረውን የቅዱስ ጊዮርጊስን ጠንካራ የመከላከል አወቃቀርን ለመስበር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ84ኛው ደቂቃ ሱሌይማን ሀሚድ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ተጠቅመው የአብስራ ተስፋዬ እና ቸርነት ጉግሳ አከታትለው ያደረጓቸው እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከማዕዘን ምት ከተሻማ ኳስ ያደረጓቸው እና አቡበከር ኑሪ ያዳናቸው ኳሶች በአጋማሹ ተጠቃሽ የነበሩ ሙከራዎች ነበሩ።

ጨዋታውን 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፋቸውን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥባቸውን ወደ 23 በማሳደግ ሊጉን መምራታቸውን ሲቀጥሉ ባህርዳር ከተማ በ14 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።