ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የሊጉ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲቀጥሉ ነገ በቅድሚያ የሚደረገውን ጨዋታ እንዲህ ተመልክተነዋል።

በመካከላቸው የአንድ ነጥብ ልዩነት ኖሮ የሚገናኙት ሁለቱ ተጋጣሚዎች በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎቻቸው የተቃረኑ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። አምስት ጨዋታዎችን በአቻ ያጠናቀቀው አዳማ ከተማ ባህር ዳር እና ሰበታ ላይ ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ ወደ ላይ ከፍ ማለት ሲችል አራት ጨዋታዎችን በመደዳ በመርታት ደካማ አጀማመሩን መቀልበስ ጀምሮ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በሀዲያ ሆሳዕና እና ሀዋሳ ከተማ ተሸንፎ ከሰንጠረዡ አጋማሽም ወረድ ብሏል። በመሆኑም በነገው ጨዋታ አዳማ ተከታታይ ድሉን አስቀጥሎ ወደ መሪዎቹ ይጠጋል ወይስ ኢትዮጵያ ቡና ዳግም ለማንሰራራት ይጠቀምበታል የሚለው ተጠባቂ ይሆናል።

አዳማ ከተማ ሰበታን የረታበት ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ከማሳካት ሌላ ስኬትን ያስመዘገበበትም ነበር። ከዚህ ቀደም በአራት ጨዋታዎች ቀድሞ ግብ የተቆጠረበት ቡድኑ ከአቻ የዘለለ ውጤት ይዞ መውጣት ተስኖት ቢቆይም ሰበታ ላይ ይህን ደካማ ጉዞ ያቋረጠበትን አጋጣሚ ፈጥሯል። ይህ በራሱ ተጫዋቾች በራሳቸው ላይ ያላቸውን ዕምነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በየጨዋታው ላይ በግብ መቀደማቸው ራሱን የቻለ የቤት ሥራ ይሆናል። በተለይም ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥርን በመያዝ በትዕግስት ቀዳዳዎችን ለማግኘት ከሚጥረው ኢትዮጵያ ቡና ጋር በቅድሚያ ግብ ካስተናገዱ በውጤት ለመስተካከል ሲያደርጉ የሚታዩት በስሜት የተሞላ የማጥቃት ጥረት ለተጋጣሚያቸው ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ዕድል ይኖረዋል። 

ሽንፈት ባስተናገደባቸው ሁለቱ ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት የተሳነው ኢትዮጵያ ቡና  ይህ ችግሩ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በኩልም ተገልጿል። አሰልጣኙ ከሀዋሳው ሽንፈት በኋላ ከተጋጣሚዎች አቀራረብ አንፃር  ሁሌም ቢሆን ለቡድናቸው ግብ ማስቆጠር ቀላል እንደማይሆን አንስተው ነበር። ይህ ሀሳብ በነገው ጨዋታ ላይ እንዳይንፀባረቅም ኢትዮጵያ ቡና ውጤት ይዞ በወጣባቸው ወቅቶች በማጥቃት ሂደቱ በቁጥር በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ማድረስ የሚችልባቸውን ስትራቴጂዎች በአግባቡ መተግበር የግድ ይለዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ የሚቋረጡ ኳሶችም እንዲሁ ቡድኑን ሲያጋልጡት የተስተዋለባቸው አጋጣሚዎች ካልታረሙ ለአዳማ በሮች መከፈታቸው አይቀርም።

አዳማ ከተማ ከኳስ ውጪ ቅብብሎችን የሚያቋርጡ እንደአማኑኤል ጎበና ዓይነት አማካዮችን ከመያዛቸው ባለፈ የዳዋ ሆቴሳ ጥሩ አቋም ላይ መገኘት እና የአብዲሳ ጀማል ወደ ግብ አስቆጣሪነት መምጣት በነገው ጨዋታ በፍጥነት ሳጥን ውስጥ ለመድረስ እና ግቦችን ለማግኘት እገዛ ሊያደርግላቸው ይችላል። ኢትዮጵያ ቡና ግን ዋነኛው አጥቂ አቡበከር ናስርን የሚጠቀምበት ዕድል ባለመኖሩ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮቹ በአዳማ መሀል እና መስመር ተከላካዮች መሀል ያለውን ቦታ ለመክፈት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ዘግየት ብለው የሚደርሱ እንደዊሊያም ሰለሞን ያሉ ተጫዋቾቹን ብቃት ይፈልጋል።

በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና ከደቡብ አፍሪካ ትናንት የተመለሳው አቡበከር ናስርን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን አዳማ ከተማ ግን በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች አይኖርም።

 
ባህሩ ተካ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ሲመደቡ ረዳቶቻቸው የሆኑት ደግሞ ትግል ግዛው እና ሶርሳ ዱጉማ ሆነዋል። በተጨማሪ ኃይለየሱስ ባዘዘው የጨዋታው አራተኛ ዳኛ ናቸው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች 38 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 21 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አዳማ ከተማ በበኩሉ 7 ጊዜ ድል ሲቀናው በ10 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 68 ፤ አዳማ 34 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ጀሚል ያዕቆብ – ሚሊዮን ሰለሞን – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ዮሐንስ

አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው

አብዲሳ ጀማል – ዳዋ ሆቴሳ – አሜ መሐመድ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረተንሳይ – አበበ ጥላሁን – ቴዎድሮስ በቀለ – ሥዩም ተስፋዬ

ሮቤል ተክለሚካኤል – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊልያም ሰለሞን

አቤል እንዳለ – እንዳለ ደባልቄ – አስራት ቱንጆ

ያጋሩ