[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ከነገ የሊጉ ጨዋታዎች የምሽቱን መርሐግብር የተመለከተው ዳሰሳችን እንዲህ ይነበባል።
ውድድሩ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ሲዘዋወር በሽንፈት ከጀመሩ ቡድኖች መካከል የሆኑት ፋሲል እና ሰበታ ነገ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። የዓመቱን ሁለተኛ ሽንፈታቸው በቅርብ ተፎካካሪያቸው እና በሰፊ የጎል ልዩነት የደረሰባቸው ፋሲል ከነማዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸው ልዩነት ወደ አምስት ከፍ በማለቱ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ከፉክክሩ እንዳይርቁ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። በሌላ በኩል የውጤቱ አስፈላጊነት ለሰበታ ከተማ ይበልጥ ዋጋ አለዉ። በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው ቡድኑ ከበታቹ ያለው ጅማ አባ ጅፋር በማሸነፉ እና ነጥባቸውም በመስተካከሉ በቀጣይ በሰንጠረዡ ግርጌ ሊገኝ የሚችልበት ዕድል በመስፋቱ ነገ ውጤት ይዞ የመውጣት ግዴታ ውስጥ ይገባል።
የውጤቱ አስፈላጊነት ተጋጣሚዎች ጨዋታውን ጥንቃቄ በታከለበት አቀራረብ እንዲቀርቡት ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ በፊት ማሸነፍ ባልቻለባቸው ጨዋታዎች ማግስት በተለየ ብቃት ወደ ሜዳ የሚመለሰው ፋሲል ከነማ ዘንድሮ ይህ ጠንካራ ጎኑ የከዳው ይመስላል። በአዲስ አበባ ከደረሰበት ያልታሰበ ሽንፈት በኋላ ሁለት አቻዎችን ማስመዝገቡም ለዚህ ማሳያ ነው። ሙሉ ለሙሉ ደካማ የውድድር ዓመት ላይ የሚገኘው ሰበታ ከተማም ቢሆን ከእስካሁን አካሄድ ከሽንፈት መልስ ይበልጥ ጫና ውስጥ ገብቶ ይታይ እንደሆነ እንጂ በተለየ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ የሚገባበት ዕድል ሰፊ አይደለም። ከዚህ አንፃር በጠባብ ልዩነትም ቢሆን ውጤትን ማግኘት የተጋጣሚዎች ዋና አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ፋሲል ከነማዎች በጊዮርጊሱ ጨዋታ ጠንካራ ጎኖቻቸውን ሁሉ አጥተው ነበር። ግለሰባዊ ስህተቶች የተበራከቱበት ተነሳሽነቱም ከወትሮው ወርዶ ከታየበት ካዛ ጨዋታ ነገ በብዙ መልኩ ተሻሽሎ መገኘት ይኖርበታል። ቡድኑ ግቦችን ለማስቆጠር በሚሄድበት ወቅት ከሚሰሩ ስህተቶች የተገኙ ኳሶች በቀላሉ ከተከላካይ መስመር ጀርባ የሚተወው ክፍት ቦታ ላይ ደርሰው አደጋ ሲጥሉነት ታይቷል። የአስቻለው እና ያሬድ ብሔራዊ ቡድኑ የኋላ መስመር ጥምረት በፋሲል ቤት የተጠበቀውን ጥንካሬ መጨመር አልቻለም። በተለይም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ብልጫ ሲወሰድበት መታየቱ ፋሲል በደካማው የሰበታ የፊት መስመርም ሊፈተን እንደሚችል የሚጠቁም ነው።
በእርግጥ ፋሲል ከጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ በፈጣን ጥቃት ጉዳት ደርሶበታል። ሆኖም የነገ ተጋጣሚው ሰበታ ከተማ ተመሳሳይ እርምጃ ወስዶ ዕድሎችን የመፍጠር ብቃቱ አስተማማኝ የሚባል አይደለም። በኳስ ቁጥጥር ወደፊት ለመሄድ ሀሳብ ያለው ሰበታ ከወገብ በላይ ባለው ቡድኑ ላይ ተደጋጋሚ ለውጦችን ሲያደርግ ቢቆይም ትክክለኛው ስሌት ላይ የደረሰ አይመስልም። እንደ አክሊሉ ዋለልኝ እና መሀመድ አበራ ዓይነት ተጫዋቾች ከረጅም ጊዜ ጉዳት መመለሳቸው ለአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ዕረፍት የሚሰጥ ቢሆንም ቡድኑ በፍጥነት በሚፈለገው የውህደት ደረጃ ላይ ደርሶ የነገውን ከባድ ተጋጣሚውን ያስጨንቃል ይሚለው ሀሳብ በጥርጣሬ የሚታይ ነው። ኳስ መስርቶ ከሜዳ በመውጤት እና ተጋጣሚን በማስከፈት ረገድም ተመሳሳይ እስቤ ያለው ፋሲል ብልጫ ሊወስድበት ይችላል።
ፋሲል ከነማ አምበሉ ያሬድ ባየህን በጉዳት ምክንያት ሲያጣ ሀብታሙ ተከስተ ቀለል ያለ ልምምድ መጀመሩን ሰምተናል። በሰበታ ከተማ በኩል ግን የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና አልተሰማም።
ይህንን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ማኑሄ ወልደፃዲቅ ሲሆኑ በረዳትነንት ይበቃል ደሳለኝ እና ትንሳኤ ፈለቀ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ተካልኝ ለማ ተመድበዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች ከተሰረዘው የውድድር ዓመት ውጪ ሁለት ጊዜ (አምና) በሊጉ ተገናኝተው ሁለቱንም በአቻ ውጤት (1-1 እና 0-0) አጠናቀዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)
ሚኬል ሳማኬ
ዓለምብርሃን ይግዛው – አስቻለው ታመነ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው
ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ
ኦኪኪ አፎላቢ
ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)
ለዓለም ብርሀኑ
ጌቱ ኃይለማሪያም – ቢያድግልኝ ኤሊያስ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
ክሪዚስቶም ንታምቢ – አክሊሊ ዋለልኝ
ሳሙኤል ሳሊሶ – አንተነህ ናደው – ዱሬሳ ሹቢሳ
መሀመድ አበራ