“ሁሉን ነገር ተቆጣጥረናል በጨዋታም የበላይ ነበርን” አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ
“የእኛን እንቅስቃሴ ያለን ነጥብ ስለ እውነት አይገልፀውም” አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ
በምሽቱ ጨዋታ መቻል በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ሀምበሪቾን 1ለ0 በማሸነፍ የሊጉን ተከታታይ ድል ካሳካበት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የድህረ ጨዋታ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ – ሀምበሪቾ
ስለ ጨዋታው…
“ጨዋታው መጥፎ አይደለም ጥሩ ነበር ፣ አጋጣሚዎችንም ፈጥረናል ጥሩ ነው ጨዋታው ተመጣጣኝ ነው በሁለታችን በኩል።”
ባለፉት 5 ጨዋታዎች ቡድኑ ሜዳ ላይ ከሚያሳየው እንቅስቃሴ አንፃር ሁለት ነጥብ ብቻ ስለማግኘቱ …
“እንዳያችሁት ነው በፍፁም አይገልፀውም። የእኛን እንቅስቃሴ ያለን ነጥብ ስለ እውነት አይገልፀውም ፣ ከዚህ በላይ ነጥብ መያዝ ይገባን ነበር እንደ እንቅስቃሴ እግር ኳስ ነው ፤ ቀስ እያለ እየተሰራ የመጣ ቡድን ነው ፣ ምናልባት ጥሩ ነው ዛሬ ከሌላው ጊዜ ደግሞ የተሻለ ነበር። መቻል ጠንካራ ክለብ ነው ግን እንደዛም ሆኖ ጥሩ እንቅስቃሴ ነበረን።”
በጨዋታው ስላቀረቡት የፍፁም ቅጣት ምት ይገባል ጥያቄ…
“የዳኛው ዕይታ ነው ፣ በዕርግጥ ይመስላል ከሩቅም ሳየው ምክንያቱም አንድ ስቴፕ ሄዷል እርሱ እና ያው እዛ አካባቢ የሚሰሩ ጥፋቶች ፔናሊቲ ነው ብዬ አስባለሁ።”
በቀጣዩ ዕረፍት ለማስተካከል ስለሚያስቡት ነገር…
“ዕረፍታችንን ብዙ የወዳጅነቶችም ማድረግ አለብን እንደገና ደግሞ የአጨራረስ ጥንቃቴ ፣ ብዙዎቹ የሱፐር ሊግ ልጆች ናቸው። ምንአልባት ዛሬ ከተጫወቱት ውስጥ ሁለት ተጫዋቾች ብቻ ናቸው የፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች እና ያንን በጨዋታ ፊትነሳችንን አስተካክለን የቀሩም ተጫዋቾች አሉ እነርሱን በጨዋታ ጥሩ በማሰልጠን በዕርግጠኝነት የተሻለ ቡድን ይዘን እንመጣለን።”
አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል
በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ማሸነፋችሁ እንደ ባለፈው ጨዋታ ዕድለኛ ናችሁ ማለት ይቻላል..
“አይደለም ፣ ሁሉን ነገር ተቆጣጥረናል በጨዋታም የበላይ ነበርን እና ይሄ ጎል ብቻ አይደለም መሆን የነበረበት። ጥሩ ነው ማሸነፋችን ዋናው ሦስት ነጥብ ማሳካት ነው። እግር ኳስ ዘጠና ደቂቃ ተጨማሪም አለው እስከዛ ሁሉንም ማድረግ አለብህ። በአጠቃላይ ቡድናችን ዘጠና ደቂቃ የመጫወት አቅም እንዳለው ነው የሚያሳየው ፣ ከባንክ ጋር ብታይ እንደዚሁ በዘጠና ደቂቃ አካባቢ ነው ያገባነው ፣ ይሄ የሚያሳየው የተጫዋቾች እስከ መጨረሻ አልሸነፍ ባይነት ውስጣቸው መኖሩን እና ለማሸነፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል።”
በሁለተኛው አጋማሽ ሽመልስ በቀለ ተቀይሮ ስለ መውጣቱ…
“ጉዳት ነው። ዳዊትም እርሱም በጉዳት ነው የቀየርናቸው ፣ ምክንያቱም ድካም አለ ሦስት ቀን ነው ያረፍነው ፣ ተጫዋቾች ባለፈው ዘጠና ደቂቃ በኢንቴንሲቲ ነው የተጫወቱት ፣ በዛ ምክንያት ትንሽ ጡንቻው ላይ ጉዳት ስለነበረ በዚህ ምክንያት እንዲያርፍ ፈልገናል። ለረጅም ጊዜ ልናጣው ስለ ማንፈልግ።”
ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ ጎሉን ስላገባው ያሬድ ከበደ እና አሰልጣኙ ስላሳዩትም የተለየ የደስታ አገላለፅ…
“ወደ ውስጥ ሲገባ ያሬድ ነው ጎሉን የሚያገባው ብያቸዋለሁ እና ያ ነገር መከሰቱ ነው በጣም ደስ ያለኝ ምክንያቱም ልጁ እንዲነሳሳ እንፈልጋለን ፣ ኳሊቲ ያለው ተጫዋች ነው አሁን በጥሩ ጊዜ መጥቶልናል ማለት ነው። እኛ እንደውም የጠበቅነው ወደ ስድስተኛው ጨዋታ ከዕረፍት በኋላ ነበር ይደርሳል ብለን የጠበቅነው ፣ ተጫዋቹ ባለው ቁርጠኝነት ደርሶልናል ኳሊቲ ያለው እንደ ሽመልስ ኳስ ጠንቅቆ የሚጫወት ስለሆነ ሽመልስን በምናጣበት ሰዓት እርሱ ይጫወትልናል ማለት ነው ፣ ለዛም ነው ያስገባሁት አምኜበት ነው።”
እስከ አሁን ባለው የአምስት ሳምንታት ጨዋታ ቡድኑ በሚፈለገው ደረጃ እየሄደ ነው ብሎ ማለት ይቻላል…
“አንድ ቡድን እኮ የሚታወቀው ቢያንስ ከስምንት ጨዋታ በኋላ ነው። አሁን ደግሞ እንደገና ሊቋረጥ ነው ፣ ኢንተንሲቲያችን ይወርዳል እንጂ አሁን እንደፈለግነው አይደለም ግን ፍንጮች አሉ የሚታዩ ማለት ነው ፣ ወደዛ እየሄድን ነው ተከታታይ ጨዋታዎችን በሚያገኙበት ሰዓት የተሻለ ደረጃ ቡድኔ ይመጣል ብዬ አስባለሁ።”