የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ዋንጫ ለመዳኘት ሁለት ኢትዮጵያውያን ዳኞች ወደ ዩጋንዳ ያመራሉ።
በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከጥቅምት 24 እስከ ኀዳር 6 ድረስ ለሚካሄደው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ዋንጫ የፊታችን ቅዳሜ ስምንት ሀገራትን አሳትፎ እንደሚጀመር ይጠበቃል። ሴካፋ ለውድድሩ 9 ዋና እና 9 ረዳት ዳኞችን ከአባል ሀገራቱ የመረጠ ሲሆን በመሃል ዳኝነት ሄኖክ አበበ ፣ በረዳት ዳኝነት ደግሞ ወጋየሁ አየለን ከኢትዮጵያ አካቷል፡፡ ሄኖክ ባሳለፍነው ዓመት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ አንድ ጨዋታ የዳኘ ሲሆን ረዳት ዳኘው ወጋየሁ ደግሞ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታውን በተደጋጋሚ መዳኘቱ ይታወሳል። በዚህም የዳኞች ኮሚቴ የኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ልምድ እንዲያገኙ እንደላካቸው ተገልጿል።
በሌላ ዜና ለውድድሩ ኢንስትራክተር እና ገምጋሚ በመሆን ከተመረጡት አራት ባለሙያዎች መካከል ኢትዮጵያዊው በላቸው ይታየው ወደ ስፍራው እንደሚያቀና ታውቋል።