የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 3-0 ሰበታ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ፋሲል ከነማ ሰበታ ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱም አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ዕቅድን ስለመተግበር

“በመሰረቱ በባለፈው የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ላይ ብዙ ያጣናቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዛ መሙላት አለባቸው። በዛ ልክ መገኘት አለብን ባክ ቱ ባክ ቻምፒዮን ለመሆን እያንዳንዱ ጨዋታ ፈተና ነው፡፡ እና የጊዮርጊሱ ጨዋታ ብዙ አስተምሮናል ፤ እሱ ላይ ብዙ ብለናል። ለዚህም ነው ዛሬ ይሄ ለእኛ ትልቅ መነሻ ነው። ምክንያቱም አሁን ከሚመራን በቅርብ ርቀት ላይ መሄድ አለብን። የሚቀጥሉትን ጨዋታዎች ደግሞ በጥንካሬ ለመውጣት ወደ አሸናፊነት ሥነ ልቦና ዳግም መመለስ አለብን። ስለዚህ ዛሬ ያደረግነው ነገር ጥሩ ብዬ ነው የሚስበው፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የታየው ፋሲል እና በዛሬው ዕለት ስለ ነበረው ፋሲል

“ምን መሰለህ ከጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት እነሱ በመጡበት መንገድ ሞቲቬሽናቸው ፣ አንድ ለአንድ ስንገናኝ ፣ በመከላከል በማጥቃት የነበራቸው ተነሳሽነት የተሻለ ነበር፡፡ያንን ዕድል ነው የሰጠናቸው በዛም በጎል ቀደሙን። በኋላ ከእዛ ለመነሳት ብዙ የተቸገርንባቸው ነገሮች አሉ። ስለዚህ እያንዳንዱን ጨዋታ ትኩረት ሰጥተን እንድንሄድ አሁንም ስንጀምር የመጀመሪያ አስር አስራ አምስት ሀያ ደቂቃ ድረስ ሰበታ ከተማ ጥሩ ነበር። በተለይ መሀል ሜዳ ላይ የነበሩ ልጆቻችን በእንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይገቡ የሚያደርጉት ማርኪንግ እኛ ወደ ረጃጅም ኳስ እንድናደላ አድርጎናል። ደግሞም የሚጠቅመን አልነበረም እና የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች ከፍተው እንዲጫወቱ ራሳቸውን ነፃ እንዲያደርጉ ወደ ጨዋታ እንዲገቡ በዛም ልክ እየተነጋገርን ስንመጣ የነበረው ነገር እየለቀቃቸው ወደ ጥሩ ሪትም መጥተዋል። ጥሩ ጨዋታ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡

 

ስለ በረከት ደስታ አቋም

“በረከት ብዙ ጊዜ ደጋግሜ ብዬዋለሁ ልጁ ካለፈው ዓመት በጣም በእጥፍ የጨመረ ነገር አለው። እጥፍ የጨመረው አቅሙ አለው ፣ ኃይሉ አለው ፣ ሁሌ ወደ ሳጥን ነው የሚሄደው ፣ ጨዋታዎቹ ሁሌም ለጎል መነሻ የሚሆኑ ናቸው ፣ የሚደክም ሰው አይደለም ፣ በጣም ታጋይ ልጅ ነው። ለቡድናችን ደግሞ ጥሩ ነገር እያደረገ ነው። ከቡድን አጋሮቹ ጋር ሆኖ በዚህ አቅሙ ብዙ ከሄደ ሽልማቶችን የሚያገኝበት መንገድ ሰፊ ነው፡፡

አሁንም ሻምፒዮን ስለመሆን

“አምና ቻምፒዮና የሆነ ቡድን ለምን አንደግመውም ያሉት ልጆች እንዳሉ ናቸው። ከመካከላችን የጨመርናቸው ልጆች አሉ። ስለዚህ በዚህ ስሌት መሄድ መቻል አለብን። በቀላሉ አገኛለሁ ብለህ ማሰብ ሳይሆን እየሰራን እንሄዳለን ፤ እያሻሻልን እንሄዳለን። እንደገና ሻምፒዮን ለመሆን ደግሞ የሁላችንም ከክለቡ ጀምሮ አጠቃላይ ደጋፊዎቻችን ጥረት ያስፈልጋል። እዚህም የኛ ተጫዋቾች ያላቸው ስሜት በዛ ልክ ስለሆነ ለዛም እንሮጣለን ፤ እንታገላለን፡፡

ስለ ተጫዋቾች ትጋት ደስተኛ ስለመሆን

“አዎ በጣም ደስተኛ ነኝ ምክንያቱን ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ነገር ሳምንቱን ያሳለፍነው ጊዜ በጣም የከፋ ቀን ነው። ለምን ? እንዴት ሆነ ? የሚለው ነገር ለራሳቸው ጭምር ነው ደወል የሰጠው። ስለዚህ ተነሳሽነታቸው ያደርጉት የነበረው እያንዳንዱ ጥሩ ሄዶልናል ብዬ ነው የማስበው። ግን ከዚህ በላይ ማደግ መጀመር አለብን በእያንዳንዱ ጨዋታም የሚፈለገው ይሄ ነው፡፡ ቻምፒዮን የሚሆን ቡድን ብዙ ቻሌንጆች ይገጥሙታል። ይሄንን ለመወጣት ከዚህ በላይ መገኘት አለብን፡፡”

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ሰበታ ከተማ

ስለ ውጤቱ

“ለሽንፈቱ ምክንያት ራሳችን ነን። ምክንያቱም ጨዋታውን እንዳየህው ጠንካራ ጨዋታ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ከዛም በተረፈ ደግሞ ይበልጥ የኛን ድክመት የሚያጎላውም የተነጋገርንባቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ከጨዋታው በፊት የቆሙ ኳሶችን ፍፁም መጠንቀቅ እንዳለብን አውርተናል። ግን ሦስቱም ጎሎች የተቆጠሩብን ከቆሙ ኳሶች ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የቆሙ ኳሶችን የመከላከል አቅማችን በጣም ደካማ ስለነበር የራሳችን ድክመት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

በርከት ያሉ የተከላካይ ሚና ያላቸው ተጫዋቾች ኖረው የቆመ ኳስ ስለ መቆጠሩ

“በነገራችን ላይ አምስት የመስመር ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ሦስት የመሀል ተጫዋቾችነት ሚና የነበራቸው ሦስት ደግሞ ፈጣሪ የሚባሉ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የመስመር ተሻጋሪ ኳሶችን የመቆጣጠር አቅማችን ደካማ እንደነበር ያሳያል። ይሄን ግን የሚያጎላው ሁለት የማዕዘን ምቶች ናቸው። ሁለት የማዕዘን ምቶች ሲገቡ የኮሚዩኒኬሽን ችግር ነበር ፤ መነጋገር አልተቻለም። ሰውንም ማርክ ማድረግ አልተቻለም። ከዛ ውጪ በእንቅስቃሴ ረገድ ከዚህ ቀደም ተጋጣሚያችን እንደሚታወቅበት እንደፈለገ የመስመር ጨዋታዎችን ማድረግ አልቻለም ፤ ያንን ማቆም ችለናል። በተቃራኒው እነኚህ የቆሙ ኳሶችን መከላከል አልቻልንም። ለዛም ነው የቆሙ ኳሶችን ለመከልከል የመስመር ተጫዋቾችን በአብዛኛው ለመጠቀም የፈለግነው ነገር ግን ፍላጎት እና ድርጊት የተለያዩ ናቸው፡፡”