[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ከድል የተመለሱን ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።
የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየት ሊግ የጀመረባት ከተማ ሀዋሳ እና የአሁኗ የውድድሩ መካሄጃ ድሬዳዋ ክለቦች የሆኑት ተጋጣሚዎች ዘጠነኛው ሳምንት ላይ ድል ቀንቷቸው ነበር። ሁለት ተከታታይ ድል ያሳኩት ሀዋሳዎች ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥቦችን ማግኘት ወደ ሊጉ መሪዎች ጊዮርጊስ እና ፋሲል የሚያቀርባቸው በመሆኑ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው። ተመሳሳይ ሁለት ድሎችን አጣጥመው ለዚህ ጨዋታ የደረሱት ድሬዎችም ቢሆኑ ደካማ አካሄዳቸው በማረሙ ለመቀጠል እና ከሰንጠረዡ ወገብ ወደ ላይ ለመጠጋት ማሸነፍ አስገላጊያቸው ይሆናል።
ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች 13 ነጥቦች ያሳኩት ሀዋሳዎች ነገሮች እንዳሰቡት እየሄዱላቸው ይመስላል። ያለፉት ተጋጣሚዎቻቸው የጨዋታ ባህሪ የተራራቀ መሆን እና በአመዛኙ ውጤት ይዘው መውጣታቸውም በእንቅስቃሴ በምን መንገድ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው እየተረዱ ስለመሆናቸው ፍንጭ ይሰጣል። የነገው ተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ ከተማን ስንመለከት ለኳስ ቁጥጥር የሚያደላ በመሆኑ ሀዋሳዎች በቡና ላይ የተገበሩት አጨዋወት ላይ መጠነኛ ማሻሻያ ብቻ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ያሳየናል። በዛ ጨዋታ ወደ ግራ ባደላ ፈጣን ሽግግር የተጋጣሚያቸውን ቅብብሎች እያቋረጡ በቶሎ ግብ ላይ ይደርሱ የነበሩት ኃይቆቹ የመስመር አጥቂዎቻቸውን ከኳስ ውጪ በጥልቀት ወደ ኋላ ስበው ከኳስ ጋር ደግሞ በቶሎ ወደ ሳጥን እንዲቀርቡ ሲያደርጉ ይታይ ነበር። ነገ ግን ነገ እነዚህን የቡድኑ ዋና የማጥቃት መሳሪያዎች ከኳስ ውጪም በተወሰኑ ሜትሮች ወደ ፊት የተጠጋ አቋቋም እንዲኖራቸው ሊያደርጉ ይችላሉ።
ድሬዳዋ ከተማ በአሰልጣኝ ዘማሪያም ጊዜም ሆነ አሁን ላይ ባሉት ጊዜያዊ አሰልጣኙ ፉዓድ የሱፍ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን እንዲይዝ ይፈለጋል። ሆኖም ቡድኑ በዚህ መልክ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በቅብብሎች ከሜዳው ለመውጣት ሲጥር ቢታይም በትዕግስት እስከመጨረሻው ከመዝለቅ ይልቅ ቀጥተኛነትን ሲቀላቅል ይስተዋላል። ለዚህም ባስላፍነው ሳምንት አብዱልፈታ ዓሊ የተሰለፈበት እና እስካሁን አራት የሚደርሱ ተጫዋቾች የተፈራረቁበት የአስር ቁጥር ሚናው ሁነኛ ሰው አለማግኘት አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንፃር ቡድኑ ነገም የሜዳውን አጋማሽ በቅብብሎች ከተሻገር በቶሎ ኳስ ወደ ፊት ለማድረስ እንደሚጥር ይጠበቃል።
ተጋጣሚዎቹ በሁለት ዘጠና ደቂቃዎች ግብ ሳይቆጠርባቸው ለነገው ጨዋታ መድረሳቸው ለአጥቂዎቹ የቤት ስራ የሚሰጥ ነው። በሀዋሳ በኩል በእነመስፍን ታፈሰ እንደዘበት የሚሳቱ የግብ ዕድሎች ጠንካራ መከላከል ሲገጥማቸው እና በቁጥር ሲያንሱ የግብ ማስቆጠር ንፃሪያቸው እንዳይወርድ ያሰጋል። የድሬዳዋ ከተማ የአማካይ ክፍልም እንደተጋጣሚው የግብ ዕድሎችን በብዛት መፍጠር እና ከእስካሁኑ በተሻለ የግብ አበርክቶት ሊኖራቸው የሚገባቸው አጥቂዎቹን ማገዝ ይጠበቅበታል።
ሀዋሳ ከተማ ከዚህ ጨዋታ በፊት በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች ሳይኖር ለነገው ጨዋታ ደርሷል። ድሬዳዋ ከተማ ግን ጋዲሳ መብራቴ እና ብሩክ ቃልቦሬ በጉዳት ሲያጣ እንየው ካሳሁን ከጉዳት መመለስም አጠራጣሪ ሆኗል። ከዚህ ውጪ ጋናዊው አውዱ ናፊዩ እስከ አሁን ከሀገሩ ያልተመለሰ በመሆኑ በመከላከያው ጨዋታ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ወጣቱ አቤል አሰበ አሁንም ዕድል እንደሚያገኝ ሲጠበቅ ሌላኛው ጋናዊ አብዱለጢፍ መሀመድ ግን ከቅጣት መልስ ቡድኑን እንደሚያገለግል ይጠበቃል።
ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ የመሀል ዳኝነት ሲከወን ካሳሁን ፍፁም እና ፍሬዝጊ ተስፋዬ ረዳቶች እንዲሁም አሸብር ሰቦቃ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 18 ጊዜ ሲገናኙ ሀዋሳ ስድስት ድሬዳዋ ደግሞ አምስት ጊዜ ድል አድርገው በቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ኃይቆቹ 17 ጎሎችን ሲያስመዘግቡ ብርቱካናማዎቹ 16 ጎሎች አሏቸው።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (4-2-3-1)
መሀመድ ሙንታሪ
ዳንኤል ደርቤ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – መድሀኔ ብርሀኔ
አብዱልባስጥ ከማል – በቃሉ ገነነ
ኤፍሬም አሻሞ – ወንድማገኝ ኃይሉ – መስፍን ታፈሰ
ብሩክ በየነ
ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)
ፍሬው ጌታሁን
እንየው ካሳሁን – አቤል አሰበ – መሳይ ጳውሎስ – ሄኖክ ኢሳይያስ
ዳንኤል ደምሴ – ዳንኤል ኃይሉ
አብዱርሀማን ሙባረክ – ሙኸዲን ሙሳ – አብዱለጢፍ መሀመድ
ማማዱ ሲዲቤ