[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ከሽንፈት የመጣው አዲስ አበባ እና ከድል መልስ ራሱን ያዘጋጀው ወላይታ ድቻ ነገ 9 ሰዓት የሚያደርጉትን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻለው አዲስ አበባ ከተማ በሰንጠረዡ በ7 ደረጃዎች እና በ5 ነጥቦች የሚበልጠውን ዲቻን ነገ በመፋለም ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ከፍ ለማለት ድልን እያሰበ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታመናል።
በጊዜያዊ አሠልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ የሚመራው አዲስ አበባ ከተማ ከሦስተኛ እስከ ስድስተኛ ሳምንት የነበረበትን የውጤት መነቃቃት አሁን ላይ ማስቀጠል እየተሳነው ይመስላል። በተለይ ከመከላከያ፣ ፋሲል፣ አዳማ እና ሀዲያ ጋር የነበረው ጠንካራ ቡድናዊ አጨዋወት ያለፉትን አራት ጨዋታዎች እየተቀዛቀዘ ይመስላል። ቡድኑ ከመከላከያ እና ፋሲል ከተማ ጨዋታ ውጪ ከአንድ በላይ ጎል ማስቆጠሩ እና ከዛ በኋላ በተደረጉት ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ጎል ብቻ ማስቆጠሩ ሲታሰብ መጠነኛ መዳከም ላይ ያለ ይመስላል። ከምንም በላይ ደግሞ የማጥቃት አማራጮቹ ውስን መሆናቸው ለተጋጣሚ ቡድኖች በቀላሉ የሚተነበይ አድርጎታል።
በዋናነት በፍፁም የመስመር እንቅስቃሴ ላይ የተገደበ የጎል ምንጭ ለማግኘት ሲጥር የሚታየው አዲስ አበባ በነገው ጨዋታ ሲከላከልም ሆነ ሲያጠቃ በቁጥር በርከት ብሎ የሚታየውን ድቻን ማስከፈቻ ሁነኛ መላ መዘየድ የሚጠበቅበት ይመስላል። የማጥቃት ስትራቴጂውን አማራጭ ከማስፋት ባለፈ ደግሞ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ፈጥሮ በተጋጣሚ ሳጥን ዙሪያ የሚያደርጋቸው ደካማ ቅብብሎች ዕድሎችን ከመጠቀም አግደውታል። ይህንን የጎል ፊት ችግር ቀርፎ ከመጣ ግን አዎንታዊ ውጤት ሊያገኝ እንደሚችል ይታሰባል። ከዚህ ውጪ በጅማው ጨዋታ የቡድኑ የአማካይ መስመር ከኳስ ውጪ ለኋላ መስመሩ የሚያደርገው ድጋፍ በመጠኑ መሳሳቱ ግቡ እንዲጋለጥ እና ጅማ በላይኛው ሜዳ እንዲጫወት አስችሎት ነበር። ናይጄሪያዊው አማካይ ቻርለስ ሪባኑ ከጉዳቱ ማገገሙ ደግሞ ለዚህ ክፍተት መፍትሄ የሚሰጥ ይመስላል።
አራት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት አካባቢ የነበረው ወላይታ ድቻ በቀጣዮቹ አራት ጨዋታዎችን ካለማሸነፍ ከተጓዘ በኋላ አርባምንጭ ላይ ያገኘውን ሦስት ነጥብ ዳግም ነገም ለማግኘት ጠንካራውን ፈተና ማለፍ ይጠበቅበታል።
በዘንድሮ የውድድር ዓመት በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ መሪ ከነበሩ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ድቻ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ጠንካራ ሆኖ ፍልሚያዎችን ያሸነፈባቸው ጨዋታዎችን በወጥነት አለመዝለቃቸው ነው እንጂ ከሁለተኛ ጀምሮ እስከ ስድስተኛ የጨዋታ ሳምንት ድረስ በውጤትም ሆነ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ዕድገት እያሳየ ሳይጠበቅ ተፎካካሪ ሆኖ ነበር። ይህ ፉክክር ግን እንደ ፋሲል፣ ባህር ዳር፣ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ አይነት በሊጉ ጠንካራ የሆኑ ቡድኖችን ሲገጥም አልደገም ብሎ መጠነኛ የውጤት መፋዘዝ አጋጥሞት ነበር። በ10ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ደግሞ ያ ታታሪነታቸው እና ሜዳን አካሎ መጫወት እንዲሁም እንደ ቡድን አጥቅቶ የመከላከል ባህሪን ደግመው ከፍፁም ቅጣት ምት ቢሆንም ወሳኝ ሦስት ነጥብ ከደርቢያቸው አርባምንጭ አግኝተዋል።
በአርባምንጩ ጨዋታ ያለ ወሳኝ አጥቂው ስንታየሁ መንግስቱ ወደ ሜዳ ገብቶ የነበረው ቡድኑ ነገ ቁመታሙን ተጫዋች ሊያሰልፍ እንደሚችል ይገመታል። በዚህም ስንታየውን ያማከለ ረጃጅም ኳሶች በመላክ የጎል ምንጭ ለማግኘት እንደሚጥርም ይታሰባል። እምብዛም ለኳስ ቁጥጥር ቦታ የማይሰጠው ድቻ ነገም በዚሁ ባህሪው እንደሚጫወት ሲገመት ምናልባት ፈጣን የማጥቃት አጨዋወትም በሁለቱ መስመሮች በኩል ሊሰነዝር ይችላል። ይህ ቢሆንም ግን ከላይ እንደገለፅነው የአዲስ አበባም የመስመር አጥቂዎች ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ ጥሩ መላ መያዝ ይገባዋል።
በአዲስ አበባ በኩል የተከላካይ አማካዩ ቻርለስ ሪባኑ ከጉዳቱ ተመልሶ ቡድኑን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑ ሲገለፅ ነብዩ ባልጉዳ እና ፈይሰል ሙዘሚል አሁንም ከጉዳታቸው አላገገሙም። ወላይታ ድቻ ደግሞ አናጋው ባደግን ብቻ በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት አያሰልፍም።
9 ሰዓት ሲል የሚጀምረውን ጨዋታ ኤፍሬም ደበሌ በመሐል አልቢትርነት ሲመሩት ተመስገን ሳሙኤል እና አብዱ ይጥና የረዳት ዳኞች ሄኖክ አክሊሉ ደግሞ አራተኛ ዳኛ እንዲሆኑ መመደቡን አውቀናል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 2 ጊዜ (2009) ተገናኝተው የመጀመርያውን አዲስ አበባ ከተማ 1-0 ሲያሸንፍ ሁለተኛውን ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል ተሾመ
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ልመንህ ታደሰ – ዘሪሁን አንሼቦ – ያሬድ ሀሰን
ኤልያስ አህመድ – ቻርለስ ሪባኑ – ሙሉቀን አዲሱ
እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ አዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን
ወላይታ ድቻ (4-3-3)
ወንድወሰን አሸናፊ
ያሬድ ዳዊት – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – በረከት ወልደዮሐንስ
እድሪስ ሰዒድ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሐብታሙ ንጉሤ
ቃልኪዳን ዘላለም – ስንታየሁ መንግስቱ – ምንይሉ ወንድሙ