[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ በቃልኪዳን ዘላለም የመጨረሻ ደቂቃ ጎል አዲስ አበባ ከተማን 2-1 ረትቷል።
አዲስ አበባ ከተማ ከጅማው ሽንፈት ልመንህ ታደሰ ፣ ብዙአየሁ ሰይፈ እና ሪችመንድ ኦዶንጎን በኤልያስ አህመድ ፣ ቻርለስ ሪባኑ እና የሽዋስ በለው በመተካት ወደ ሜዳ ገብቷል። ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ቅጣት ባገኘው አናጋው ባደግ ምትክ አጥቂያቸው ስንታየሁ መንግሥቱን ተጠቅመዋል።
ጨዋታው በጀመረባቸው ቅፅበቶች ስንታየሁ መንግሥቱን ያማከሉ ቀጥተኛ ኳሶች የጦና ንቦቹን የበላይ አድርጓቸው ነበር። ሆኖም ቀስ በቀስ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመያዝ ወደ ቀኝ አድልተው ወደ ድቻ ሳጥን መቅረብ የጀመሩት አዲስ አበባዎች የጨዋታውን ከባባድ ዕድሎች ፈጥረዋል። 10ኛው ደቂቃ ላይ የሽዋስ በለው ከፍፁም ጥላሁን ተቀብሎ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው እንዲሁም ኤልያስ አህመድ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ከየሽዋስ ደርሶት ከሳጥን ውስጥ ያደረጓቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን የጠበቁ እና በወንድወሰን አሸናፊ ጥረት የዳኑ ነበሩ።
የአዲስ አበባዎች የኳስ ቁጥጥር ወደራሳቸው ሜዳ የገፋቸው ድቻዎች ግን ባልታሰበ ሁኔታ ወደ ሳጥን በላኩት ኳስ ቀዳሚ ሆነዋል። 20ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ጉግሳ ከመሀል ሜዳ ያሻማውን ኳስ ስንታየሁ መንግሥቱ ሳጥን ውስጥ ተቆጣጥሮ በመዞር ወደ ግብነት ለውጦታል። በእርግጥ አጥቂው ኳሱን ሲቆጣጠር በእጅ ነክቶ የነበረ ቢሆንም ከዳኞች እይታ ውጪ ሆኖ ጎሉ ፀድቋል።
ከውሀ ዕረፍቱ በኋላ ጨዋታው ወደ ተመጣጠነ ፉክክር መጥቷል። ድቻዎች ከመስመር እና ከመሀል ሜዳ ወደ ፊት የሚልኳቸው ኳሶችም አልፎ አልፎ አደጋ ሲፈጥሩ ይታዩ ነበር። በተለይም ምንይሉ ወንድሙ በመስመር እና መሀል ተከላካዮች መሀል ተሰንጥቆ የደረሰውን ኳስ ከቀኝ ያሻማበት አጋጣሚ አደገኛ ሁኔታ ቢፈጥርም ዳንኤል ተሾመ ጨርፎ አውጥቶታል። የመዲናው ቡድንም ከቀደመው በፈጠነ መልኩ ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥር 33ኛው ደቂቃ ላይ የሸዋስ ከሳጥን ውጪ ባደረገው እና ወንደወሰን አሸናፊ ባወጣው ሙከራ እንዲሁም 39ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ጥላሁን በአስደናቂ ሁኔታ ተከላካዮችን አልፎ ከሳጥን ውጪ ግብ አፋፍ ድረስ በመግባት ወደ ግብ የላከው ኳስ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ ቢታይም አዲስ አበባዎች አቻ ለመሆን ተጭነው ለማጥቃት ሞክረዋል። ሆኖም የድቻዎች መከላከል ከሚያስገኛቸው የቆሙ ኳስ ዕድሎችም አዲስ አበባዎች መጠቀም ሳይችሉ ቆይተዋል። 62ኛው ደቂቃ ላይ ግን በፍፁም ጥላሁን እና አሰጋኸኝ ጴጥሮስ አንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ የፈጠረውን ዕድል በአጋማሹ ተቀይሮ የገባው ሪችሞንድ ኦዶንጎ ወደ ግብ ሲልከው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የቆየው ወንድወሰን እግሮች መሀል ገብቷል።
ወላይታ ድቻዎች በስንታየሁ አማካይነት ወዲያውኑ ምላሽ ለመስጠት የሞከሩባቸው አጋጣሚዎች ባይሳኩም የጨዋታው ቀሪ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክርን እያስመለከተን የቀጠለ ነበር። ያም ሆኖ ቡድኖቹ ንፁህ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ጨዋታው ወደ ጭማሪ ደቂቃዎች ቢያመራም ወላይታ ድቻዎች ግብ ቀንቷቸዋል። በጭማሪው አራተኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በተቃራኒ ቦታ ነፃ ሆኖ የቆመው ቃልኪዳን ዘላለም በቀጥታ ወደ ግብ መትቶት የድቻን አሸናፊነት ያበሰረች የመጨረሻ ደቂቃ ጎል አስቆጥሯል።
ውጤቱን ተከትትሎ ወላይታ ድቻ ደረጃውን ከስድስት ወደ ሦስት ከፍ ማድረግ ሲችል አዲስ አበባ ከአደጋ ዞን መራቅ የሚችልበትን ዕድል አምክኗል።