ባህርዳር ከተማን ከፋሲል ከነማ ያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ 0-0 ተጠናቋል።
የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በባህር ዳር ከተማ እና በፋሲል ከነማ መካከል ሲደረግ ባህርዳሮች ወልቂጤን ከረቱበት አሰላለፍ አደም አባስ እና አባይነህ ፊኖን በማስወጣት ከጉዳት በተመለሱት ፍሬው ሠለሞን እና ቸርነት ጉግሳ ሲተኳቸው ፋሲሎች የኢትዮጵያ ቡና ድላቸው ላይ የተጠቀመበትን አሰላለፍ ሳይቀይሩ ለጨዋታው ቀርበዋል።
9 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛው በአምላክ ተሰማ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግበትም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመድረሱ በኩል ፋሲሎች የተሻሉ ነበሩ። 9ኛው ደቂቃ ላይም ጋቶች ፓኖም በሰነጠቀለት ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ የደረሰው አማኑኤል ገብረሚካኤል ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያሬድ ባዬህ በጥሩ ቦታ አያያዝ አቋርጦበታል።
በሚያገኙት ኳስ በመስመር የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ላይ ተመስርተው በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን መጠጋት የቻሉት ዐፄዎቹ የመጨረሻ ኳሳቸው ግን ፈታኝ አልነበረም። ሆኖም ግን 26ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገብረሚካኤል በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ አሻግሮት በፍጥነው የደረሰው መሳይ አገኘሁ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።
ከራሳቸው የግብ ክልል በርካታ ቅብብሎችን በማድረግ ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ በአጋማሹ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ግን በተሻለ ግለት ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮችን አድርገዋል። በዚህም ፍጹም ጥላሁን ፣ ያሬድ ባዬህ እና ቸርነት ጉግሣ ፈታኝ ያልሆነ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።
ጨዋታው 44ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ በአጋማሹ የተሻሉት ትዕይንቶች ታይተውበታል። በዐፄዎቹ በኩል ሱራፌል ዳኛቸው ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ምኞት ደበበ እና መናፍ ዐወል ሳያገኙት ቀርተው የግብ ዕድሉን ሳይጠቀሙበት ሲቀሩ በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ባህርዳሮች ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። ፍጹም ጥላሁን ከግብ ጠባቂው ሳማኬ ሚኬል ጋር ተገናኝቶ ለማለፍ ሲሞክር ከግብ ጠባቂው ጋር በተፈጠረው ንክኪ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ወርቃማውን የግብ ዕድል አባክኖታል። ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማም አጨቃጫቂ በነበረው አጋጣሚ ጥፋት የተሠራበት የሚመስለውን ፍጹም ጥላሁንን አስመስለህ ወድቀሃል በሚል ቢጫ ካርድ በሚሰጥበት ቅፅበት በጣና ሞገዶቹ በኩል ከፍተኛ ቅሬታ ተሰምቷል።
ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ባህርዳር ከተማዎች ተሻሽለው በመቅረብ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን መውሰድ ችለዋል። ሆኖም ግን የመጀመሪያው ንጹህ የግብ ዕድል በዐፄዎቹ በኩል ተፈጥሯል። ሱራፌል ዳኛቸው ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ለመግጨት ምቹ ቦታ ሆኖ ያገኘው ቃልኪዳን ዘላለም በደካማ አጨራረስ አባክኖታል።
በጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተጋጣሚን የግብ ክልል መፈተን የቀጠሉት የጣና ሞገዶቹ 62ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። የአብሥራ ተስፋዬ ያቀበለውን ኳስ በግሩም ክህሎት ያመቻቸው ሀብታሙ ታደሰ ከፍ አድርጎ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኪ በድንቅ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል። ያንኑ ኳስ ፍራኦል መንግሥቱ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ሲያሻማ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ኳሱን ያገኘው ያሬድ ባዬህ በድጋሚ ወደ ውስጥ አሻግሮት ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ ከጨረፈው በኋላ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ፍጹም ጥላሁን ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።
ከነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ፋሲሎች የተጫዋች እና የአደራደር ለውጥ በማድረግ ወደ ተሻለ የኳስ ቁጥጥር የመጡ ቢመስሉም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር እየተቀዛቀዘ የሄደው ጨዋታም በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግበት ሲቀጥል 85ኛው ደቂቃ ላይ ግን የባህርዳሩ ፍራኦል መንግሥቱ ከግራ መስመር አሻምቶት የግቡን አግዳሚ ገጭቶ መልሶበታል። ጨዋታውም የተጠበቀውን ያህል የግብ ዕድል ሳይፈጠርበት ያለ ግብ ተጠናቋል።