“ሁለታችንም ካሳየነው ነገር አንፃር ነጥብ መጋራታችን ብዙም አልከፋኝም” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
“ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት ይገባን ነበር” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው
ያለ ጎል ከተጠናቀቀው የአፄዎቹ እና የጣና ሞገዱ የደርቢ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከሁለቱም አሰልጣኞች ጋር ቃለ ምልልስን አድርጋለች።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ
በአምስት ጨዋታ ሦስተኛውን አቻ ስላስመዘገቡበት ጨዋታ…
“ባለፉት ጨዋታዎች ከሀዋሳ ጋር የወጣነው አቻ እና ይሄኛው አቻ ፍፁም ተመሳሳይ አይደለም ፣ ያን ሁለት ለባዶ ከተመራን በኋላ ሦስት ለሦስት ማጠናቀቅ የቻልነው ፣ በፍፁም የሆነ መዘናጋት ዋጋ የከፈልንበት ጨዋታ ነው። ይሄኛው ግን በጣም ጠንካራ ጨዋታ ነው ፣ በሁለታችን በኩል ጥሩ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ነው ስለዚህ እንደዚህ አይነት ጨዋታዎች በተጨማሪ የደርቢነት ስሜት አለ ፣ በዚህ አይነት ጨዋታ በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ብዙ መጥፎ አይደለም። ሁለታችንም ካሳየነው ነገር አንፃር ነጥብ መጋራታችን ብዙም አልከፋኝም።”
ከመጀመሪያው አጋማሽ የማጥቃት ባህሪ በሁለተኛው አጋማሽ ወርደው መቅረባቸው እና ቡድኑም ስላጣው ነገር ….
“መጀመሪያ ላይ ብዙ ዕድሎችን አግኝተናል ፣ ትንሽ ጥንቃቄ ብናክልበት ወደ ጎልነት መቀየር የሚችሉ ተደጋጋሚ ዕድሎችን አግኝተን ነበር። ከዛ በኋላ ግን ባህርዳሮች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ መግባት ችለዋል ፣ ከእነርሱ የሚመጣውንም ጫና ለመቋቋም በእኛ በኩል የሚቻለውን ጥረት አድርገናል። ምንአልባት ከስድስት ቀን በፊት ያደረግነው ሌላው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተጫወትነው ጨዋታ ብዙ ፊዚካል ትግል የነበረው ጨዋታ ነው። ስለዚህ ከዛ አንፃር ይመስለኛል ተከታታይ ጠንካራ ጨዋታዎችን ያደረግነው ኢትዮጵያ ቡና ጥሩ የሚጫወት ፣ ጥሩ ስብስብ ፣ ጥሩ ተጫዋቾች ያሉበት ቡድን ነው ከእነርሱ ጋር ዘጠና ደቂቃ የነበረን ትግል ከባድ ነው። ይሄኛውም ሁለተኛ ተከታታይ ከባድ ጨዋታ ነው ፣ ያ ይመስለኛል በሁለተኛው አርባ አምስት ቡድኑ ላይ መቀዛቀዞችን ያየነው ፣ በአጠቃላይ ግን መጥፎ አልነበረም። የመጀመሪያ አጋጣሚዎችን ተጠቅመን ቢሆን ጨዋታውን ይዘን የመውጣት ዕድላችን ሰፊ ነበር።”
በቀጣይ ከሚኖረው ዕረፍት በኋላ ምን አይነቱን ፋሲል ከነማ እንጠብቅ…
“ወር አካባቢ ፣ ሀያ ሰባት ቀን ገደማ ሊጉ ይቋረጣል ፣ ግን እኛም ቢሆን በመሐል የኢትዮጵያ ዋንጫ ሌላ ውድድርም ስላለ እዛ ውድድር ላይ እንሳተፋለን። በሂደት እስከ አሁን ያለው ነገር ጥሩ ነው አዲስ ቡድን አይደለም ፣ ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻልን ለመምጣት እየሞከርን ነው። ባየናቸው ክፍተቶች ላይ ደግሞ የመስሪያ ጥሩ ጊዜ ይሆነናል ብዬ አስባለሁ።”
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ
ስለ ጨዋታው…
“ጠንካራ ጨዋታ ነው ፣ ተጋጣሚያችን ፋሲልም ጠንካራ ስብስብ ያለው ነው። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች የተካተቱበት ነው የእኛም ተጫዋቾች በሜዳው ላይ ማድረግ የሚገባቸውን አድርገዋል ብዬ ነው የማስበው ፣ የተሻለ የግብ ዕድሎችን የፈጠርንበት ሁኔታ ነው የነበረው ዞሮ ዞሮ ሦስት ነጥብ ይዘን መውጣት አልቻልንም በአቻ የተጠናቀቀ ውጤት ነው። ተጫዋቾቻችን ለሰጡት ሜዳው ላይ ላደረጉት ነገር በሙሉ ትልቅ አክብሮት ነው ያለኝ።”
የፍሬው ሠለሞን እና ቸርነት ጉግሳ ከጉዳት ድነው ወይንስ ጨዋታው አስፈላጊ ከመሆነ አኳያ…
“ከጉዳት ለማገገም የእነርሱ ጥረት ተጨምሮበት ለጨዋታው ደርሰውልናል። ከሚገባውም በላይ ደቂቃ በሜዳው ውስጥ ተጠቅመንባቸዋል ፣ ጨዋታውም ላይ ያስፈልጉን ስለነበር። ሜዳው ላይ እንዳየህው እንቅስቃሴ ዛሬ ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት ይገባን ነበር ዕድሎችንም ፈጥረን ነበር ነገር ግን ደርቢ ጨዋታ የራሱ የሆነ ስሜት ፣ የራሱ የሆነ የጨዋታ መንፈስ አለው። ተጫዋቾቻችን ያንን በአግባቡ ለመቆጣጠር ሞክረዋል ፣ አንዳንዴ ደግሞ ከአቅም በላይ የሆኑ ነገሮች ሲከሰቱ ትቀበላለህ።”
የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄ ይገባናል ስለ መባሉ…
“ይሄንን በተመለከተ ተመልካች ነው ሊመስክር የሚገባው ፣ እኛ ሜዳ ላይ ሆነን በምናደርገው ጨዋታ ሙሉ ትኩረታችን እንቅስቃሴው ላይ ነው የሚሆነው ፣ እንግዲህ ዳኛው የተመለከተበት የራሱ መንገድ ሊኖር ይችላል ግን ይገባን ነበር ብዬ አስባለሁ። ሆኖም ግን የዳኞች ውሳኔ ምንድነው የሚለውን እነርሱ ናቸው የሚያውቁት በተረፈ ግን ጠንካራ ጨዋታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ውጤት የሚቀይሩ ናቸው እና ምንአልባትም የጨዋታው ሂደት በዚህ መልክ አይቋጭም ነበር ብዬ አስባለሁ።”
እስከ አሁን ስለ ነበሩት የአምስት ሳምንት ጨዋታዎች እና ስለ ዋንጫ…
“ገና ነው። አሁን ስለ ዋንጫ ምናምን የምናወራበት አይደለም ብዬ አስባለሁ ፣ ረጅም ጉዞ ነው። ዛሬም የተገኘንበት ቦታ ባለፈውም ስንጀምር የነበርንበት ቦታ ላይ ነው በአምስቱ ሳምንት ጨዋታ ያንን ለማሻሻል ነበር ጥረት ያደረግነው በአንድ ሆነ በሌላ መንገድ አልተሳካልንም። ዞሮ ዞሮ ለቀጣይ ጊዜያት ከዕረፍት መልስ የተሻለ ቡድን ሰርተን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ። እስከ አሁን በመጣንበት መንገድ ጤናማ የሆነ ጉዞ እየተጓዝን ነው ፣ ተጫዋቾቻችን አመሰግናለሁ ማለት ነው የምፈልገው።”
በክለብ እና በብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝነት ወቅት ምን ተጠቀምኩ ምንስ ተጎዳው ብለህ ታስባለህ…
“የተሰጠኝን ሀገራዊ ግዴታ በአግባቡ ተወጥቻለሁ ብዬ አስባለሁ። ምንም የአጭር ጊዜ ቆይታ ቢሆንም በተሰጠን አቅማችን የፈቀደውን በሙሉ ለማድረግ ሞክረናል። ምን ተጠቀምክ ለሚለው ጥሩ ልምድ አግኝቼበታለሁ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ብዙ ከተደከመ ከተሰራ ብዙ ነገሮችን ማሳካት እንደሚቻል ያየሁበት ነው። ተጎዳውት የምለው ነገር አይኖርም ምንአልባት እንደ ቡድን ስትመለከተው ግለሰቦች የየራሳቸው አስተሳሰብ እና ምንከታ ይኖራቸዋል። የክለቤን ስራ በማይነካ መልኩ ነው ብሔራዊ ቡድን ላይ የሰራውት ፣ ሆኖም ግን በወቅቱ ከመመረጥ አለመመረጥ ከብሔራዊ ቡድን ጋር ተያይዞ የተለያየ ስሜት ያጫሩ ተጫዋቾች እንደነበሩ ኋላ ላይ መረዳት ችያለሁ ይሄ ደግሞ ሰዋዊ ባህሪ ነው። እንደ ሀገር ግን ሀገራዊ ግዴታዬን ተወጥቻለሁ ፣ እንደ ግለሰብ ደግሞ ልምድም አግኝቼበታለሁ ብዬ አስባለሁ።