[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ሦስት ግቦችን ባስተናገደው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስቶ ድሬዳዋ ከተማን 3-2 ድል አድርጓል።
ሀዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፈበት ጨዋታ ባደረገው ብቸኛ ለውጥ አማካይ ክፍል ላይ ዳዊት ታደሰ በአብዱልባስጥ ከማል ምትክ ተሰልፏል። ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ መከላከያን ከረታበት ጨዋታ ጉዳት የገጠመው እንየው ካሳሁን ፣ አብዱልፈታ ዓሊ እና ማማዱ ሲዲቤን በዐወት ገብረሚካኤል ፣ ቢኒያም ጥዑመልሳን እና ከቅጣት በተመለሰው አብዱለጢፍ መሀመድ ተክቷል።
በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ጨዋታቸውን የጀመሩት ድሬዳዋዎች ከሌላው ጊዜ በተሻለ ቅብብሎችን በመከወን እና የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም በመሞከር ሲያጠቁ ይታዩ ነበር። በአንፃሩ ሀዋሳዎች ከኳስ ውጪ የነበራቸው እንቅስቃሴ አደገኛ የሆኑባቸውን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች እየጠበቁ እንደነበር የሚያሳይ ነበር። በዚህ ሁኔታ ያለጠንካራ ሙከራዎች በዘለቀው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች ቀዳሚ ሆነዋል።
17ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም ጥዑመልሳን የሰነጠቀለትን ዐወት ገብረሚካኤል በቀኝ በኩል ወደ ውስጥ ይዞ በመግባት ሲይሳልፍለት አብዱርሀማን ሙባረክ በግንባር ወደ ግብ የላከውን ኳስ የሀዋሳው ተከላካይ መድኃኔ ብርሀኔ ለማውጣት ባደረገው ጥረት በራሱ ላይ አስቆጥሯል።
ከግቡ በኋላ ሀዋሳዎች አቻ ለመሆን ጫና መፍጠር ጀምረዋል። የቡድኑ ቀጣይ የግብ ዕድል ግን ከቆመ ኳስ የተገኘ ነበር። 24ኛው ደቂቃ ላይ ላውረንስ ላርቴ ከዳንኤል ደርቤ የማዕዘን ምት ኢላማውን የጠበቀ የግንባር ኳስ ሙከራ አድርጎ ፍሬው ጌታሁን አድኖበታል። ይሁን እንጂ በአንድ ደቂቃ በኋላ በቃሉ ገነነ ከድሬ ተከላካዮች ጀርባ ያደረሰውን ግሩም ኳስ ወንድምአገኝ ኃይሉ የቅብብሉን ጥራት በሚመጥን አጨራረስ ግብ አድርጎታል።
አጋማሹ እስኪገባደደ በጥሩ ፉክክር በቀጠለው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል። ድሬዎች የኳስ ቁጥጥሩን በቀደመው መልኩ ማስቀጠል ባይችሉም በሙኸዲን ሙሳ አማካይነት 29ኛው እና 33ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን ጥቃት ዕድሎችን አግኝተዋል። የመጀመሪያውን ሙኸዲን ከቅርብ ርቀት ሞክሮ ወደ ውጪ ሲወጣበት በሁለተኛው አጋጣሚ መድኃኔ ደርሶ በሸርተቴ ከእግሩ ስር ወስዶበታል። በሀዋሳዎች በኩል 39ኛው ደቂቃ ላይ ወንድምአገኝ ግብ ባስቆጠረበት አኳኋን የተቀበለውን ኳስ ከቀኝ አቅጣጫ ለመስፍን ቢያሳልፍለትም መስፍን ወደ ግብ ለመቀየር ያደራገውን ጥረት ዳንኤል ኃይሉ ተደርቦ አድኖታል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ሀዋሳዎች በፍጥነት ግብ አፋፍ ደርሰው ተቀይሮ የገባው ተባረክ ሄፋሞ ለወንድምአገኝ አድርሶለት አማካዩ ያደረገውን ሙከራ ፍሬው ጌታሁን አድኖበታል። በዚህ የጀመሩት ሀዋሳዎች በእንቅስቃሴ የበላይነቱን ወስደው በአመዛኙ በድሬዳዋ ሜዳ ላይ መቆየት ችለዋል። ሆኖም ለመልሶ ማጥቃት ቀርቦ የታየው የድሬዳዋ አቀራረብ በቀላሉ ክፍተቶችን አልሰጠም። ድሬዎችም አልፎ አልፎ ወደ ፊት በመሄድ ጥቃቶችን ቢሰነዝሩም ጨዋታው ንፀህ የግብ ዕድል ሳይታይበት ቆይቷል።
ከውሀ ዕረፍቱ መልስ ጨዋታው ሲጋጋል ዳግም ብልጫቸውን ያገኙት ድሬዎች የአጋማሹን አደገኛ ሙከራ አድርገዋል። 76ኛው ደቂቃ ላይ የሄኖክ ኢሳይያስ ወደ ቀኝ ያደላ የርቀት ቅጣት ምት በላውረንስ ላርቴ ተጨርፎ ወደ ግብ ሲያመራ መሀመድ ሙንታሪ ለጥቂት አድኖታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ መሳይ ጳውሎስ ከድሬዳዋ ሜዳ ያሻማውን ኳስ ግን ፀጋሰው ድማሙ በአግባቡ ሳያወጣው አግኝቶ አብዱለጡፍ መሀመድ ግብ አድርጎታል። ድሬዎች ወዲያው በሳሙኤል ዘሪሁን ከሳጥን ውጪ ባደረጉት ሙከራም ለሦስተኛ ግብ ተቃርበው ነበር።
ሀዋሳ ከተማዎች ለጎሉ የሰጡት ምላሽ ግን እጅግ አስገራሚ ነበር። 84ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደርቤ ያሻማውን የማዕዘን ምት ተባረክ ሄፋሞ በግንባሩ ሲሞክር መስፍን በደረቱ አብርዶ በመቀስ ምት ከመረብ አገናኝቶ ጨዋታውን ወደ አቻ አምጥቶታል። መስፍን በድጋሚ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርሮ የመታው ኳስም ሦስተኛ ግብ ከመሆን የዳነው በግቡ አግዳሚ ነበር። በዚህ ያላበቁት ሀዋሳ ከተማዎች ጭማሪ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት በተነሳ እና ድሬዎች በአግባቡ ካላራቁት ኳስ ቸርነት አወሽ ከግቡ አፋፍ ላይ ባስቆጠረው ጎል በአስገራሚ ሁኔታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው ሊወጡ ችለዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ነጥቡን 20 በማድረስ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።