[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የ11ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በወላይታ ድቻ አንድ ለምንም የተሸነፈው አርባምንጭ ከተማ ከስድስት ጨዋታዎች በፊት ካገኘውን ድል ጋር ለመታረቅ ነገ ብርቱ ትግል እንደሚያደርግ ይታሰባል።
በአሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው ቡድኑ በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ በመከላከያ ከተረታ በኋላ ሲያደርጋቸው የነበሩት ጠንካራ እንቅስቃሴዎች ቀስ በቀስ እየወረዱ የመጡ ይመስላል። በተለይ ደግሞ በቡድናዊ መዋቅር ሜዳን አካሎ መጫወት፣ ታታሪነት፣ ተጋጣሚን በቶሎ ኳስ መንጠቅ እና ፈጣን ሽግግሮችን በማድረግ ጎል ጋር መድረስ በአርባምንጭ በኩል እየተቀዛቀዙ መጥተዋል። ያም ቢሆን ግን በደረጃ ሰንጠረዡ የውጤት መራራቅ እምብዛም ስለሌለ በቶሎ ከግርጌው ለመራቅ ነገ ማጥቃት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት ተከትለው ወደ ሜዳ ሊገቡ እንደሚችሉ ይገመታል።
የሊጉ ሁለተኛው ትንሽ ጎል ያስቆጠረ ክለብ የሆነው አርባምንጭ (ከጅማ ጋር እኩል 7) ጎል ፊት ከፍተኛ ችግር እንዳለበት በጉልህ እየተስተዋለ ይገኛል። ካደረጋቸው አስር ጨዋታዎችም ከአንድ በላይ ግብ ያስቆጠረባቸው ፍልሚያዎች ሁለት ብቻ ናቸው። ግቦችን ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን ደግሞ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይም ክፍተቶች ይታዩበታል። በድቻው ጨዋታም በተወሰነ መልኩ ኬኒያዊውን አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶን ወደ መስመር በማውጣት እስካሁን ያልሞከሩትን የማጥቃት አጨዋወት ለመከተል ቢጥሩም የተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ እየተገኙ የግብ ዕድሎችን በአጥጋቢ ሁኔታ መፍጠር ግን አልቻሉም ነበር። ይህንን ተከትሎም በርከት ያሉ ኳሶችን ከሳጥን ውጪ ወደግብነት ለመቀየር ሲጥሩ ነበር። በአንፃራዊነት ካፓይቶ በተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል ተሻጋሪ ኳሶች እንዲነሱ ቢደረግም ውጥናቸው በረጃጅሞቹ የድቻ ተከላካዮች ሲመክን ነበር። ይህ ቢሆንም ራሱ ካፓይቶን ጨምሮ ሀቢብ ከማልን የመሳሰሉ ቀልጣፋ እና ስል ተጫዋቾች አሁንም ቡድኑ ውስጥ ስላሉ በፍጥነታቸው የሲዳማን ተከላካዮች የራስ ምታት ሊሰጧቸው ይችላል።
ከአዳማ ከተማ ቀጥሎ በሊጉ በርካታ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ያገባደደው ሲዳማ ቡና (5) ደግሞ ባገኘውን የአሸናፊነት ጉዞ ለመዝለቅ እና በተከታታይ ያሸነፋቸውን ጨዋታዎች ቁጥር ወደ ሦስት ለማሳደግ ነገ ከአርባምንጭ የሚጠብቀውን ፈተና ማለፍ ይገባዋል።
በአስረኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማን ከመመራት ተነስቶ ያሸነፈው ሲዳማ ቡና በጥሩ ሞራል ላይ ያለ ይመስላል። በእንቅስቃሴ ደረጃም በማጥቃት እና በመከላከሉ ረገድ ካለፉት ጨዋታዎች መጠነኛ እድገት እያሳየ ይገኛል። ከምንም በላይ ደግሞ ከወገብ በላይ የሚዋልል አጨዋወት በመከተል የተጋጣሚን የተከላካይ ክፍል ትኩረት ለመበታተን የሚያደርጉት ጥረት ድንቅ ነበር። 2-1 ባሸነፉበት ጨዋታም ከፍ ብሎ ለመከላከል የሚጥረውን የጣናው ሞገዶቹ የኋላ መስመር ከፊቱ እና ከጀርባው ቦታዎችን ለማግኘት ሲውተረተሩ ታይቷል። በዋናነት ደግሞ ከይገዙ አጠገብ ሀብታሙ አጥቦ እንዲጫወት ተደርጎ በተጨማሪም ነፃ ሚና የተሰጠው ፍሬው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሦስተኛ ሰው ሩጫን እንዲያደርግ በማድረግ የግብ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ተደርጎ ነበር። በነገው ጨዋታም ይህ የጨዋታ መንገድ ከተደገመ አርባምንጮች ሊቸገሩ ይችላሉ።
ሲዳማ ቡና በዘንድሮ የውድድር ዘመን አልቀረፍ ያለው ክፍተቱ ለተከላካዮች ተገቢውን ሽፋን አለመስጠቱ ነው። አልፎ አልፎ በአንድ አንዳንዴ ደግሞ በሁለት የተከላካይ አማካዮች ጨዋታዎችን በሚጀምርባቸው አጋጣሚዎችም ይህ ክፍተት እየታየ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች በመስመሮች መካከል በነፃነት እንዲገኙ እና የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን እንዲፈጥሩ እያደረገ ነው። የነገ ተጋጣሚው አርባምንጭ ምንም እንኳን አዘውትሮ በመስመር የሚያጠቃ ቡድን ቢሆንም እንደዚህ አይነት ክፍተትን አግኝቶ ዝም ስለማይል ሲዳማ ማሻሻያ ካላደረገ አደጋ ሊፈጠርበት ይችላል። በተለይ ደግሞ ከኳስ ጋር ጥሩ የሆነው ሀቢብ እየተሳበ ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን አጋጣሚዎች በአግባቡ መመከት ይጠበቅባቸዋል።
በአርባምንጭ ከተማም ሆነ በሲዳማ ቡና በኩል ምንም አዲስ የጉዳት እና ቅጣት የሌለ ዜና እንደሌለ ሰምተናል። በሲዳማ በኩል ግን የመስመር ተከላካዩ ሰለሞን ሀብቴ ከጉዳቱ ቢያገግምም በጨዋታው የመሳተፍ ዕድሉ ጠባብ እንደሆነ ተገልፆልናል።
ይህንን ጨዋታ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሐል አልቢትርነት ከረዳት ዳኞቹ ሶርሳ ዱጉማ እና ትንሳኤ ፈለቀ ጋር ሲመራው ተካልኝ ለማ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድቧል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 14 ጊዜ ተገናኝተው አብላጫውን (9) ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። አርባምንጭ 3 ሲያሸንፍ ሲዳማ ቡና 2 ማሸነፍ ችሏል። አርባምንጭ 9 ፣ ሲዳማ ቡና ደግሞ 7 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)
ይስሀቅ ተገኝ
ወርቅይታደሰ አበበ – በርናንድ ኦቺንግ – አሸናፊ ፊዳ – ተካልኝ ደጀኔ
ሀቢብ ከማል – እንዳልካቸው መስፍን – አንዱዓለም አስናቀ – አሸናፊ ኤሊያስ
ፀጋዬ አበራ – ኤሪክ ካፓይቶ
ሲዳማ ቡና (4-3-1-2)
ተክለማርያም ሻንቆ
አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና
ቴዎድሮስ ታፈሰ – ሙሉዓለም መስፍን – ዳዊት ተፈራ
ፍሬው ሰለሞን
ሀብታሙ ገዛኸኝ – ይገዙ ቦጋለ