[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የ11ኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በሁለቱ የፉክክር ፅንፎች ውስጥ የሚገኙት መከላከያ እና ወልቂጤ በየፊናቸው ላለባቸው የቤት ስራ የሚሆኑ ሦስት ነጥቦችን ፍለጋ በጨዋታ ሳምንቱ ማብቂያ ይፋለማሉ። የሊጉ መልካም አጀማመሩ ትዝታ የሆነበት መከላከያ የመጨረሻ ድሉን ካሳካ አምስት ጨዋታዎች አልፈዋል። ሆኖም ባለው የነጥብ መቀራረብ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ቡድኑ ነገ በለስ ከቀናው ወደ አጋማሹ መጠጋት ይችላል። በአንፃሩ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፉ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ከበላያቸው ያሉት ቡድኖች ሁሉ ጨዋታቸውን ያደረጉ በመሆኑ ነገ ማሸነፍ ከመሪው አራት ነጥብ ርቀት ላይ ሆነው ፉክክሩን ለመቀጠል ዕድሉን እንደሚሰጣቸው በመረዳት ወደ ሜዳ ይገባሉ።
የነገው ጨዋታ በግልፅ የጨዋታ አቀራረብ ልዩነት ባላቸው ቡድኖች መካከል የሚካሄድ ነው። በጨዋታው ወልቂጤ ከተማ በኳስ ቁጥጥር መከላከያ ደግሞ በቀጥተኛ አጨዋወት ውጤት ይዘው ለመውጣት እንደሚፋለሙ ይጠበቃል። ለዚህም መከላከያ በጉዳት አጥቷቸው የነበሩ ለመልሶ ማጥቃት ምቹ የሆኑ ተጫዋቾቹ በድሬድዋው ጨዋታ ተቀይረው መግባት መቻላቸው እንዲሁም ወልቂጤ ዋና ጨዋታ አቀጣዩ አብዱልከሪም መሀመድን ነገ ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል መኖሩ ይበልጥ ሊያግዛቸው ይችላል።
መከላከያ በአጀማመሩ ላይ የነበሩ ጥንካሬዎቹን ያጣበት ጊዜ ላይ ደርሷል። በጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ለተጋጣሚ ክፍተት የማይሰጥ የነበረው ቡድኑ አሁንም ብዙ ግብ አያስተናግድ እንጂ በቀደመው ጥንካሬ ላይ ነው ማለት አያስደፍርም። አደጋ የሚፈጥሩ ረዣዥም ኳሶቹ እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮቹም እንዲሁ በቁጥር እየቀነሱ ይገኛሉ። ከሁሉም የከፋው ግን የጦሩ ግብ የማስቆጠር ችግር ነው።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት ያልቻለው መከላከያ ከተጋጣሚ ተከላካዮች ስህተት የሚገኙ አጋጣሚዎችን ሁሉ ሲያባክን ይታያል። በእርግጥ በአንድ አጥቂ በሚመራው የፊት ክፍሉ ላይ የኦኩቱ ኢማኑኤል ከጉዳት ማገገም አንድ ተስፋ ቢሆንም ቡድኑ ከሌሎች ተሰላፊዎቹም ግቦችን ይጠብቃል። ለዚህም የቀደመ የፈጣን ሽግግር ጥንካሬውን መልሶ በማግኘት ዕድሎች ሲፈጠሩ በተፋላሚ ሳጥን አቅራቢያ ተጨማሪ ተጫዋቾች እንዲገኙ ለማድረግ መጣር ለነገው ጨዋታ እጅግ አስፈላጊው ይሆናል።
እንደመከላከያ ግብ የማስቆጠር ችግር ባይጋነንም ወልቂጤ ከተማ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ማስተናገዱ ትኩረትን የሚስብ ደካማ ጎን ነው። በቀላሉ ግብ የማይቆጠርበት የነበረው ወልቂጤ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጥቂት ግብ የማስተናገድ ደረጃን ይጋራ ነበር። እዚህ ላይ አምና በተመሳሳይ መልኩ ይህንን የመከላከል ጥንካሬ ባጣ ማግስት ገጥሞት የነበረውን የውጤት መንሸራተት ማሰብም ተገቢ ይሆናል። ምናልባት ሀኔታው ከሲልቪያን ግቦሆ ቅጣት ጋር በቀጥታ ሊያያዝ ቢችልም የመከላከል አደረጃጀቱን ማስተካከል ቡድኑ በየጨዋታው ተጋጣሚውን በግብ ብዛት ለመስተካከል የሚያወጣውን ጉልበት ሊቆጥብለት ይችላል። በተቃራኒው ከተጋጣሚው በተለየ ወልቂጤ ከፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ግቦችን በወጥነት እያገኘ መቀጠሉ በነገው ጨዋታም በጥቂት የግብ ዕድሎች ኳስ እና መረብን የማገናኘት ዕድሉን ሊያሰፋለት ይችላል።
በመከላከያ ቡድን ውስጥ ምንም የጉዳት እና ቅጣት ዜና የለም። ባለፉት ጨዋታዎች ያልነበረው ገናናው ረጋሳም ወደ አሰላለፍ ላይመለስ ቢችልም ከጉዳቱ ማገገሙ ተሰምቷል። ወልቂጤ ከተማ አሁንም ቅጣት ላይ የሚገኘው ግብ ጠባቂው ሲልቪያን ግቦሆን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን አቡበከር ሳኒ ቀለል ያለ ልምምድ ጀምሯል። ጉዳት ላይ የሰነበቱት እስራኤል እሸቱ እና አብዱልከሪም ወርቁም ወደ ቡድኑ መመለሳቸው ተስምቷል።
ጨዋታውን በመሀል ዳኝነትት የሚመሩት አርቢትር ዳንኤል ግርማይ ሲሆኑ ትግል ግዛው እና አብዱ ይጥና ረዳቶች ይሆናሉ። ማኑሄ ወልደፃዲቅ ደግሞ የጨዋታው አራተኛ ዳኛ ናቸው።
ግምታዊ አሰላለፍ
መከላከያ (4-2-3-1)
ክሌመንት ቦዬ
ልደቱ ጌታቸው – ኢብራሂም ሁሴን – አሌክስ ተሰማ – ዳዊት ማሞ
ኢማኑኤል ላርዬ – አዲሱ አቱላ
ሰመረ ሀፍተይ – ቢኒያም በላይ – ግሩም ሀጎስ
ኦኩቱ ኢማኑኤል
ወልቂጤ ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)
ሰዒድ ሀብታሙ
ተስፋዬ ነጋሽ – ዮናስ በርታ – ዳግም ንጉሴ – ረመዳን የሱፍ
ሀብታሙ ሸዋለም
ያሬድ ታደሰ – ጫላ ተሺታ
አብዱልከሪም ወርቁ
ጌታነህ ከበደ – አህመድ ሁሴን