ላለፉት ቀናት በአዲስ አበባ እና ሀዋሳ የተከናወኑት የኢትዮጵያ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ተፈፅመዋል።
በጫላ አቤ
ነቀምቴ ከተማ 3-0 ይርጋጨፌ ቡና
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በኢብሳ በፍቃዱ እና በቦና ቦካ የሚመራው ነቀምት ከተማ የጨዋታ ብልጫ ወስዶ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ መጫወት ችሏል። በይርጋ ጨፌ ቡና በኩል በጌታሁን ሸኮ እና በበረከት ሳሙኤል እየተመራ በመከላከሉ ረገድ እና ያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ሲያደረጉ ተስተውሏል። ሆኖም በ35ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ኢብሳ በፍቃዱ በግንባሩ በማስቆጠር ነቀምት ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።
ሁለተኛው አጋማሽም እንደመጀመሪያው አጋማሽ የነቀምት ከተማ የበላይነት የታየበት እና ይርጋጨፌ ቡናዎችም የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ እና የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ያስመለከተን ነበር። ነገር ግን የነቀምት ከተማን በመስመር ማጥቃት መቋቋም ሳይችሉ በ64ኛው ደቂቃ እንደ መጀመሪያው ግብ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ኢብሳ በፍቃዱ በግንባሩ በመግጨት ለቡድኑ እና ለራሱ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል። ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ በ77ኛው ደቂቃ በኢብሳ በፍቃዱ ተቀይሮ የገባው ተመስገን ዳቦ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ወደ ግብ በመቀየር ለነቀምት ከተማ ሦስተኛ ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ተጠናቆ ነቀምት ከተማ አሸናፊ መሆን ችሏል።
– በተመሳሳይ ሰዓት ሀዋሳ ላይ አርባምንጭ ከተማ ሜዳ ላይ ያልቀረቡት አቃቂ ቃሊቲዎችን በፎርፌ አሸንፎ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል።
ቡራዩ ከተማ 1-2 ቤንች ማጂ ቡና
በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም 08:00 ላይ ሁለተኛው ጨዋታ ሲጀምር በመጀመሪያው አጋማሽ በአብዱል አዚዝ አማን እና በዳግም ሰለሞን የሚመራው ቤንች ማጂ ቡና በኳስ ቁጥጥር ጥሩ የሆነ የኳስ ፍሰት አሳይቷል። ቡራዩ ከተማዎች ደግሞ በአቡበከር ጀማል እና በመሀመድ ከድር በመመራት ጥሩ በሆነ ሁኔታ በመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት በመጫወት ግብ ላለማስተናገድ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በአጋማሹ ትኩረት ሳቢ ክስትት 36ኛው ደቂቃ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ቤንች ማጂ ቡናዎች ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ ይልቅ ፈጣን አጨዋወት እና የግብ ሙከራዎችን ተመልክተናል። በ69ኛው ደቂቃ ቤንች ማጂ ቡናዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ዘላለም በየነ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ይህንንም ተከትሎ ቡራዩ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ በ80ኛው ደቂቃ ባገኙት የቅጣት ምት ናትናኤል ዳንኤል ከርቀት በማስቆጠር ቡራዩ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ በሁለቱም በኩል ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ የሆነ ጥረት እና እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ቤንች ማጂ ቡናዎች ያገኙትን የግብ ዕድል ተቀይሮ የገባው ያሬድ ወንድማገኝ አስቆጥሮ ቤንች ማጂን አሸናፊ አድርጓል።
– ሀዋሳ ላይ ሸገር ከተማ ፋሲል አስማማው እና ሀይከን ደዋሙ በሁለቱ አጋማሾች ባስቆጠሯቸው ግቦች ኦሜድላን 2-1 በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል። የኦሜድላው ኤፍሬም ቶማስ 54ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ፍፁም ቅጣት ምት ውጤቱን ከማጥበብ በዘለል ፋይዳ ሳይኖራት ቀርቷል።
ጉለሌ ክ/ከተማ 0-2 ስልጤ ወራቤ
አዲስ አበባ ላይ የዕለቱ ማሳረጊያ በነበረው ጨዋታ ቀዳሚ አጋማሽ በብሩክ ሰማ እና በማቲያስ ኤሊያስ የሚመራው ስልጤ ወራቤ በኳስ ቁጥጥር ጥሩ ፍሰት አሳይቷል። በአንፃሩ ጉለሌ ክ/ከተማ ወደኋላ በማፈግፈግ ግብ እንዳይቆጠርበት ሲጥር ተስተውሏል። ሆኖም በ20ኛው ደቂቃ በተሻገረ ኳስ ማቲያስ ኤሊያስ በግንባር በማስቆጠር ስልጤ ወራቤን መሪ ማድረግ ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽም ጉለሌዎች ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በአንፃሩ ስልጤ ወራቤዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ይህንን ተከትሎም 80ኛው ደቂቃ ላይ በተሻገረ ኳስ ማቲያስ ኤሊያስ በድጋሚ በግንባር በማስቆጠር የስልጤ ወራቤን መሪነት ማጠናከር ችሏል። ጨዋታውም በስልጤ ወራቤ አሸናፊነት ተጠናቆ ጉለሌ ክ/ከተማ ከውድድሩ ሊሰናበት ግድ ሆኗል።
– ሀዋሳ ላይ በተደረገው የመጨረሻ ጨዋታ ደሴ ከተማ የካ ክፍለ ከተማን በጉልላት ተሾመ እና ሙሉጌታ ካሳሁን ጎሎች 2-0 በመርታት ቀጣዩን ዙር መቀላቀል ችሏል።