ሪፖርት | አርባምንጭ እና ሲዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ተመጣጣኝ ፉክክር በተስተናገደበት የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና አንድ አቻ ተለያይተዋል።

አርባምንጭ ከተማዎች ወላይታ ድቻን ከረታው ስብስባቸው ውስጥ አምስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ይስሀቅ ተገኝ ፣ ወርቅይታደስ አበበ ፣ አሸናፊ ኤልያስ ፣ ሐቢብ ከማል እና ፀጋዬ አበራን አስወጥተው በምትካቸው ሳምሶን አሰፋ ፣ ደረጀ ፍሬው ፣ በሙና በቀለ ፣ ራምኬል ሎክ እና አብነት ተሾመን በመጀመሪያ ተሰላፊነት ጨዋታውን ሲያስጀምሩ ፤ በተቃራኒው ሲዳማ ቡናዎች ባህር ዳርን ከረታው ስብስብ ዳዊት ተፈራን በብሩክ ሙሉጌታ ብቻ ቀይረው ወደ ጨዋታው ገብተዋል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን በተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ አርባምንጭ ከተማዎች በሜዳው የላይኛው ክፍል ሲዳማ ቡናዎችን ጫና ውስጥ በመክተት ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ኳሶችን መስርተው ለመውጣት በመቸገራቸው ተደጋጋሚ ረጃጅም ኳሶችን ከአርባምንጭ ተከላካዮች ጀርባ በመጣል ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል።

በአጋማሹ ሲዳማ ቡናዎች ተደጋጋሚ ኳሶችን በሜዳው የላይኛው ክፍል መንጠቅ ቢችሉም ኳሶቹን ተጠቅሞ አደጋ በመፍጠር ረገድ ግን በጣም ደካማ ነበሩ። በአጋማሹም ይህ ነው የሚባል ዕድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል በአንፃሩ ሲዳማዎች በንፅፅር በኳስ ቁጥጥር ሆነ ወደ ጎል በመድረስ ረገድ የተሻሉ ነበሩ።


በ38ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ገዛኸኝ ወደ መሀል ሜዳ ከተጠጋው የአርባምንጭ ተከላካዮች ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ የአርባምንጩን ግብጠባቂ ሳምሶን አሰፋን በጥሩ አጨራረስ አሳልፎ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል።
በሁለተኛው አጋማሽም አርባምንጭ ከተማዎች የአቻነቷን ግብ ፍለጋ በአዎንታዊ ቅያሬዎች ታጅበው ቢጀምሩም እንደመጀመሪያው ሁሉ ዕድሎችን መፍጠር አልሆነላቸውም። በተቃራኒው ሲዳማዎች ደግሞ የተሻለ ኳሱን በመቆጣጠር በረጃጅም ኳሶች መነሻነት የሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች አደገኛ ነበሩ።

በተለይም በ60ኛው እና 61ኛው ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ እና ሐብታሙ ገዛኸኝ አከታትለው የሞከሯቸው እንዲሁም በ67ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ገዛኸኝ ከራሱ አጋማሽ አንስቶ በአስደናቂ ፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ይዞ ገብቶ የሞከረው እና የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ ሲዳማች መሪነታቸውን ሊያሰፉባቸው የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።

ነገር ግን በሂደት ይበልጥ በጨዋታው ተፅዕኖ እያለ የመጣው እና በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ሀቢብ ከማል የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማሻሻል ረገድ ሚና ነበረው። በ70ኛው ደቂቃ ላይም ከረጅም ርቀት አስደናቂ የቅጣት ምት ኳስ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል።
ከግቧ በኋላ ጫና ፈጥረው መጫወት ችለው የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች በ79ኛው ደቂቃ ለአርባምንጭ ከተማ የአቻነቷን ግብ ያስቆጠረው ሀቢብ ከማል መሀሪ መና ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ምክንያት ከሜዳ ሊያጡት ችለዋል።


ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በ15 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ አርባምንጮች ደግሞ በ12 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።