ሪፖርት | መከላከያ ከአምስት ጨዋታ በኋላ አሸንፏል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

መከላከያ ከአምስት ጨዋታ በኋላ ግቦች ባስቆጠረበት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማን 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል።

መከላከያ በመጨረሻው ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈትን ካስተናገደው የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች ውስጥ አቤል ነጋሽን በተሾመ በላቸው ብቻ ሲለውጥ በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ ከሀዲያ ሆሳዕና አቻ ከተለያየው ስብስብ አራት ለውጦችን ሲያደርጉ ዉሀቡ አደምስ ፣ አበባው ቦጣቆ ፣ አበባየሁ ዮሀንስ እና አብዱልከሪም ወርቁ በዳግም ንጉሴ ፣ ረመዳን የሱፍ ፣ ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ እና በኃይሉ ተሻገርን ተክተው የዛሬውን ጨዋታ ማድረግ ችለዋል።

ነቃ ያለ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ያስተናገደው ገና በ5ኛው ደቂቃ ነበር። ወልቂጤ ከተማዎች በረጅሙ ከራሳቸው አጋማሽ ከላኩት ኳስ መነሻውን ያደረገውን የኳስ ሂደት ጫላ ተሺታ ከጠበበጠ አንግል ከአብዱልከሪም ወርቁ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ጨዋታው አስር ደቂቃዎችን እንደተሻገረን ግን ከጨዋታው በፊትም የጤና እክል የነበረባቸው የቡድኑ አሰልጣኝ ጳውሎስ በሜዳ ላይ ሳሉ ህመም የገጠማቸው በመሆኑ ለተጨማሪ የህክምና እርዳታ ወደ ድሬ ክሊኒክ ተወስደዋል።

ገና ከጅምሩ ግብ ያስተናገደው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ከቀደመው የጨዋታ መንገዳቸው በተወሰነ መልኩ ለየት ያለ አቀራረብን ይዘው ተመልክተናል። መከላከያዎች ከወትሮው በተለየ መልኩ ጫና አሳድረው በመጫወት እና በቁጥር በርከት ብለው ለማጥቃት ፍላጎት ሲያሳዩ በአንፃሩ ወልቂጤዎች ደግሞ ይበልጥ ቀጥተኝነትን ጨምረው የቀረቡበት ጨዋታ ነበር። የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት በአጋማሹ ያሳዩት መከላከያዎች በ37ኛው ደቂቃ አቻ መሆን ችለዋል። ወደ ግራ ካደላ አቋቋም የተሻማውን የቅጣት ምት ሰዒድ ሀብታሙ ኳሷን በአግባቡ ማራቅ ባለመቻሉ የተገኘውን ዕድል የመጀመሪያ ጨዋታውን ለመከላከያ ያደረገው ተሾመ በላቸው ከሁለት የወልቂጤ ተከላካዮች ጋር ታግሎ ማስቆጠር ችሏል።

ተመጣጣኝ መልክን ይዞ በቀጠለው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ወልቂጤዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ በግሩም ሁኔታ ቢመታም ክሊመንት ቦዬ በአስደናቂ መልኩ አድኖበት የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ከጅምሮ ከፍተኛ ጫና አሳድረው መጫወታቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በተለይም ከቢኒያም በላይ መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶች የሰዒድ ሀብታሙን ግብ ለመፈተሽ ጥረዋል። በተቃራኒው ወልቂጤ ከተማዎችም ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እንቀስቃሴ ለመጫወት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ሂደት በአህመድ ሁሴን እና ተስፋዬ ነጋሽ አደገኛ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር።

የመከላከያዎች ጫና በመጨረሻም ፍሬ አፍርቶ በ74ኛው ደቂቃ ላይ ከደቂቃዎች በፊት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኤርሚያስ ኃይሉ በሰዒድ ሀብታሙ ስህተት ታግዞ ሁለተኛዋን ጎል ለቡድኑ ማስቆጠር ችሏል። በዚህ ያላበቁት መከላከያዎች በ87ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም ሀጎስ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታው የቅጣት ምት ኳስ ወደ ግብነት ተቀይሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሦስት ከፍ ማድረግ ችሏል።

ጨዋታው በመከላከያ 2-1 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 14 በማሳደግ 11ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በአንፃሩ ወልቂጤዎች ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን ልዮነት ሊያጠቡበት የሚችሉበትን ዕድል አበላሽተው በ16 ነጥብ 6ኛ ላይ ይገኛሉ።