[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በ11ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ መከላከያ ወልቂጤ ከተማን ድል ካደረገ በኋላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ
ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ
“እንዳያቹሁት በመጀመርያ አምስት ደቂቃ ነው የገባብን ከዛ አገግመን ተመልሰን ማሸነፍ ቀላል አይደለም። በተለይ ወጣት ምንም ልምድ የሌላቸው ተጫዋቾችን አሰልፈናል። ተሾመ የመጀመርያውን ጎል ያገባው ከወታደር ማሰልጠኛ የወጣ ከ20 ዓመት በታች ተጫዋች ነው። ፕሪሚየር ሊግ ሲጫወትም የመጀመርያው ነው። እንደነዚህ ያሉ ልጆችን ይዘን ነው የምንጫወተው። በሌላ መንገድ ዕድል እየሰጠሀቸው ነው። ዕድሉን ደግሞ መጠቀም አለባቸው። ተሾመ ከእኛ ጋር ከቆየ ገና ሁለት ወሩ ነው። አንድ ያለን የወታደር ተጫዋች ነው ፤ ሌሎቹንም ያበረታታል ብለን እናስባለን። የሚጫወተው ገና በታዳጊ ነው አረንጓዴ ካርድ ያልወጣለት ነው። ስለዚህ በአንድ ቀን ገብቶ ጫና ባለበት ውድድር ላይ ኃለፊነቱን መወጣቱ በጣም የሚመሰገን ነው።
አሸናፊነት በቀጣይ ስለማስቀጠል
“እንግዲህ ልጆቹ ላይ ነው ሁሉን ነገር የምንተወው ከሜዳ ውጭ ያለውን ስራ ፣ ልምምዱ እና ስርዓት ማስያዙ ላይ ለእኛ እንተዋለን። የጨዋታውን ሂደት ደግሞ እንደነዚህ ያሉ ልጆች እየገቡ ለምሳሌ ግሩም ፣ ብሩክ እና ኢብራሂም ከ23 ዓመት በታች ወጣት ልጅ ናቸው። እነዚህን ይዘን ልምድ እየያዙ ሲመጡ በተሻለ ኳስ ይጫወታሉ ይሄን ለማስቀጠል ነው የምናስበው።”
አሰልጣኝ እዮብ ማለ – ወልቂጤ ከተማ
ስለ ጨዋታው
“መጀመርያ ጨዋታው እንደጠበቅነው ሄዶልናል። ጎልም ማስቆጠር ችለናል። ጎል ካስቆጠርን በኋላ ረጅም ኳስ ስለሚጫወቱ ይህን ተከላክለን ኳሱን በመመለስ ይዘን ለመጫወት ነበር የተነጋገርነው ያው በጠበቅነው መንገድ አልሄደልንም።
ጨዋታው እንዳሰቡት ያልሆነበት ምክንያት
“ምክንያቱ አሰልጣኝ ጳውሎስ በሜዳ አለመኖር በሥነ ልቦናው ተፅዕኖ አድርጎብናል። ከዚህ በተረፈ በኳስ የሚያጋጥም ነው። በሁለተኛው አጋማሽ የተነጋገርነውን ስላልፈፀምን ተሸናፊ ሆነናል። ለቀጣይ ጨዋታ ሰርተን የተሻለ ነገር ይዘን እንመጣለን።
አሰልጣኝ ጳውሎስ ያሉበት ሁኔታ
“አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። እርሱም ከሜዳ ነው የወጣው ፤ ይህም በተጫዋቾቻችን ላይ ድንጋጤ ፈጥሮብናል። በእግርኳስ የሚያጋጥም ነገር ነው። ከዚህ በኋላ ጠንክረን ሰርተን ወደ አሸናፊነታችን እንመለሳለን።”