አሠልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ?

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ቡድናቸውን እየመሩ በህመም ምክንያት ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት የወልቂጤ ከተማው አሠልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው አሁናዊ የጤና ሁኔታን አጣርተናል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የመከላከያ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ በጦሩ 3-1 አሸናፊነት እንደተጠናቀቀ ይታወቃል። በጨዋታው ገና በጊዜ መሪ የነበሩት ወልቂጤዎች በ10ኛው ደቂቃ ዋና አሠልጣኛቸው ጳውሎስ ጌታቸውን አጥተው ነበር። አሠልጣኙም ቡድኑን እየመሩ ባለበት ሰዓት ከሰሞኑን ተከስቶባቸው የነበረው የታይፈስ እና ታይፎድ ህመም አቅም አሳጥቷቸው ጉልበት እንደከዳቸው በስፍራው ሆነን አስተውለናል።

አሠልጣኙም ወዲያው በቀይ መስቀል አማካኝነት የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ ድሬ ክሊኒክ የተወሰዱ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም የጤና መሻሻል እያሳዩ እንደሆነ ራሳቸውን አግኝተን አረጋግጠናል። ይህ ቢሆንም ግን አሠልጣኙ በክሊኒኩ በማደር ህክምናቸውን እንዲቀጥሉ ዶክተሮች መወሰናቸውን ያወቅን ሲሆን ምናልባትም በነገው ዕለት የጤንነት መሻሻል ካሳዩ ወደ ሆቴላቸው ሊያመሩ እንደሚችሉ ሰምተናል።

ቀድመን በሰራነው ዘገባ ላይ እንደገለፅነው አሠልጣኙ ከሰሞኑን ህመም ላይ የሰነበቱ ሲሆን ከትናንት በስትያም ልምምድ አላሰሩም ነበር። በትናንትናው ዕለትም በልምምድ መርሐ-ግብሩ ላይ ተገኙ እንጂ ሙሉ ጤነኛ እንዳልነበሩ አውቀናል። የተገኘባቸው የታይፈስ እና ታይፎድ ህመምም በዛሬው ዕለት መታወቁ እና ጉሉኮስ ተደርጎላቸው እንደነበር ተነግሮናል። በአሁኑ ሰዓትም በክሊኒኩ ጉሉኮስ እየወሰዱ ይገኛሉ።